የቀድሞ የቡናማዎቹ ኮከብ ማረፍያ . . . ?

የቀድሞ የቡናማዎቹ ኮከብ ማረፍያ . . . ?


በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል በማስቆጠር ባለክብረ ወሰኑ አቡበከር ናስር ስለ ቀጣይ ማረፍያው ፍንጭ ሰጥቷል

ያለፉትን ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ከተመለከትናቸው ድንቅ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞው የቡናማዎቹ ኮከብ አቡበከር ናስር በቀጣይ ማረፊያው ዙርያ ፍንጭ ሰጥቷል። ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው አጥቂው ከአራት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደሚመለስ አረጋግጦልናል።

በቱርክ የነበረውን አጭር ቆይታ አጠናቆ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሚገኘው ተጫዋቹ ከሳምንታት በፊት ስሙ ከደቡብ አፍሪካ ክለቦች ጋር ቢያያዝም በ2019 የውድድር ዓመት ወደ ናፈቀው ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተመልሶ ለመጫወት መወሰኑን እንዲሁም የሚመጡለትን ጥያቄዎች እያጤነ እንደሚገኝ እና በቅርቡ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚያሳውቅ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል።

በክለብ ደረጃ በሐረር ሲቲ ታዳጊ ቡደን መነሻውን በማድረግ ኢትዮጵያ ቡና በመቀላቀል ድንቅ አጥቂ መሆኑን ያሳየው አቡበከር በ2013 የውድድር ዘመን በ24 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን በማስቆጠር በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል በማስቆጠር ክብረ ወሰን በመያዝ የኮከቦች ሽልማትን ጠራርጎ በመውሰድ ባለ ታሪክ ተጫዋች መሆኑ ይታወሳል። በማስከተልም ወደ
ደቡብ አፍሪካውን ሀያል ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በማምራት ቀጥሎም በሱፐር ስፖርትስ እና ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ቆይታ ቢያደርግም ጉዳት የአቅሙን ያክል አውጥቶ እንዳይጠቀም እንደፈተነው ይታወቃል።