የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወር የሚያካሂደውን ምርጫ በተመለከተ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይፋዊ ዝግጅቱን እና የእጩዎች ጥቆማ መቀበል መጀመሩን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቋል።

የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ ዛሬ በጁፒተር ሆቴል በተሰጠው መግለጫ እንደገለጹት የፌዴሬሽኑ ምርጫ በመጪው መስከረም 5 ቀን 2019 እንዲካሄድ ተወስኗል። ከዚህ ቀደም ይካሄድ የነበረው ነጠላ የሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫ ቀርቶ ዘንድሮ ከፊፋ በተሰጣቸው ምክረ ሀሳብ የተሻሻለውን ደንብ መሰረት አድርጎ ምርጫው ፕሬዚዳንታዊ በሆነ መልኩ ብቻ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
አዲሱ የምርጫ ስርዓት እጩ ፕሬዚዳንቶች የራሳቸውን ስብስብ (ካቢኔ) ይዘው እንዲወዳደሩ የሚፈቅድ ሲሆን እያንዳንዱ እጩ ፕሬዚዳንት 1 ምክትል ፕሬዚዳንት እና ቢያንስ ሁለት ሴቶች የተካተቱበትን 7 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ቢያንስ ሁለት ሴቶች የተካተቱበትን 5 ተጠባባቂ አባላትን በአጠቃላይ 14 አባላት ያሉት ካቢኔ ይዞ ለውድድር መቅረብ እንደሚጠበቅበት ሰብሳቢው ገልጸዋል።
በምርጫው ዕለት ድምጽ የሚሰጠው ለፕሬዚዳንቱ ብቻ ሲሆን አሸናፊው ፕሬዚዳንት ከተመረጠ ያቀረበው ካቢኔ ሙሉ በሙሉ አብሮት ለአራት ዓመታት የሚቆይ ይሆናል። ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ኢትዮጵያዊ መሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በስፖርቱ ቢያንስ 5 ዓመት እና ከዚያ በላይ ያገለገለ መሆን እንደሚኖርበትም ገልጸዋል።
አቶ ኃይሉ አክለውም “የእጩዎች ጥቆማ ሰነድ ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 4 ቀን ድረስ ተሰብስቦ ለፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ገቢ የሚደረግ ሲሆን ነሐሴ 4 ቀን ታሽጎ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይረከባል። ኮሚቴው ሰነዶቹን መርምሮ መስፈርቱን ላላሟሉ ተወዳዳሪዎች የማስተካከያ 3 ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በውሳኔው ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት አቤቱታቸውን ለተቋቋመው የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ማቅረብ ይችላሉ።” ብለዋል።
ለፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ለፊፋ እና ካፍ የምርጫው መመሪያ ደንብ እና የጊዜ ሰሌዳ መላኩን የገለጹት አቶ ኃይሉ በተጨማሪም እጩዎች የራሳቸውን የውድድር ሀሳብ እና ፕሮግራም ለስፖርት አፍቃሪው የሚያስተዋውቁበት የመገናኛ ብዙኃን መድረክ እንደሚመቻች ጠቁመዋል።

