በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው መቻል በአህጉሪቱ የተለያዩ ክለቦች እየታደነ የሚገኘውን የግብ ዘብ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።
አሠልጣኝ ውበቱ አባተን የቡድኑ አለቃ አድርጎ የሾመው መቻል በዝውውር መስኮቱ የነባር ተጫዋቾችን ውል እያደሰ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ ከሀገር ውስጥ ዝውውር ፊቱን ወደ ውጪ በማዞር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም በአፍሪካ እግርኳስ በተለያዩ ክለቦች እየተፈለገ የሚገኘውን የግብ ዘብ በአንድ አመት ውል ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ጊኒያዊው መሐመድ ካማራ ነው። የ26 ዓመቱ የግብ ዘብ ካማራ በሀገሩ ክለቦች ካሉም እና ሶዋር ካገለገለ በኋላ ያለፉትን ሁለት አመታት በጋናው ኃያል ክለብ አሳንቴ ኮቶኮ ድንቅ አመት አሳልፏል። በተለይ በጋና ፕሪምየር ሊግ እያሳየ ያለውን ጥሩ አቋም ተከትሎ በዚህ ዓመት ሀገሩን በዋናው ብሔራዊ ቡድን እንዲያገለግል ጥሪ ቀርቦለት ጊኒን እያገለገለ ይገኛል። ተጫዋቹን ለማስፈረም የደቡብ አፍሪካ እና የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ጥረት እያደረጉ እንደነበረ ሲዘገብ ቢቆይም ምርጫው መቻል ሆነ ፊርማውን አኑሯል።
1.94 የሚረዝመው ካማራ ከ1998 እስከ 2013 ድረስ ሀገራቸውን በተጫዋችነት ያገለገሉት ኪሞኮ ካማራ ልጅ ሲሆን የአባቱን ፈለግ ተከትሎ በግብ ጠባቂነት እየተጫወተ ይገኛል።

