ከሰሞኑን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ መነጋገሪያ የሆነው የፕሪምየር ሊጉ የክለቦች ክፍያ ስርዓት መመሪያ መነሳት ትልቁን ቦታ የሚይዝ ሲሆን በተለያዩ አካላት ዘንድ መመሪያው መነሳቱን በተመለከተ የተለያዩ ሀሳቦች እየተሰጡ ይገኛሉ። ሶከር ኢትዮጵያም በጉዳዩ ዙሪያ መብራራት አለባቸው ብላ የምታስባቸውን ጥያቄዎች ይዛ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርነት አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ከክፍያ አሰራር አስተዳደር መመሪያ መነሳት ጋር የነበረውን ሂደት አስረዳን?
የክለቦች ክፍያ አሰራር አስተዳደር መመሪያ በወጣበት በአጭር አመታት ውስጥ ያለውን ሂደት ስናይ በመጀመሪያ ሲፀድቅ በሙሉ የአክሲዮን ማህበሩ እንዲሁም የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች በሙሉ ድምፅ ያፀደቁት መመሪያ ነው። በተከታታይ አመታት ደግሞ የሚሻሻሉ አንቀጾች እየተሻሻሉ፣ የሚጨመሩት እየተጨመሩ፣ የሚቀነሱ ካሉም እየተቀነሱ የክፍያ ጣሪያውም እንደአስፈላጊነቱ እየጨመረ የሚሄድ መመሪያ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ መሰረት እንግዲህ በ9ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ይህ መመሪያ በብቸኛ አጀንዳነት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱ ላይ ሁሉም ተሳታፊ ክለቦች ሀሳባቸውን በጥልቅ ሰጥተዋል። ከእነሱ ተሞክሮ አንፃር ምን ምን እንደነበረ በሌላው ክለብ ላይ የታያቸው አጠቃላይ በመመሪያው አፈፃፀም ላይ ሁሉም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በስተመጨረሻ ደግሞ በመመሪያው ላይ ድምፀ ውሳኔ ተሰጥቶበታል። የመጀመሪያው አማራጭ መመሪያው ባለበት ይቀጥል ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የሚሻሻሉ ካሉ ተሻሽሎ ይቀጥል ሲሆን ሶስተኛው አማራጭ ደግሞ መመሪያው ውድቅ ይደረግ የሚል ነው። በዚህ መሰረት ሁሉም መመሪያዎች በአክሲዮን ማህበሩ የሚተገበሩ መመሪያዎች በአክሲዮን አባላት ውሳኔ ሀሳብ ተሰጥቶባቸው ጸድቀው የሚሰሩ መመሪያዎች ናቸው በቢዝነስ ህጉ። ስለዚህ በአብላጫው ድምፅ ሶስቱም ላይ ድምጽ ተሰጥቶ በአብላጫው ድምፅ ‘ውድቅ ይደረግ’ ስላሉ ክለቦቹ ለ2019 ይህ መመሪያ እንዳይተገበር ውድቅ ሆኗል ማለት ነው።
የክፍያ ስርዓቱን ባለፉት 2 ዓመታት በተገቢው መንገድ እንዳይተገበር ያደረጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ብላችሁ ታስባላችሁ እንደ አክሲዮን ማኅበር?
ያው ማንኛውም መመሪያ ሲወጣ በተለይም ይህ መመሪያ ሲወጣ ሶስት አካላት አሉ። የመጀመሪያው መመሪያው በራሱ ነው፤ ሌላው አስፈፃሚ አካል፣ ሶስተኛው ደግሞ የተፈየፃሚነት ወሰኑ ነው።
ይህ መመሪያ ሲወጣ በጥናት አማራጮች ነበሩን። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ያሉ ችግሮች የትኞቹ ናቸው የሚል ከዚህ በፊት ያስጠናነው ጥናት አለ። ከጥናቱ ደግሞ አንዱን ክፍል ወስደን የክፍያ ስርዓታችን ከአፍሪካ አንፃር ሲታይ፣ ከአለም አንፃር ሲታይ ጤነኛ አይደለምና እዚህ ላይ ምላሽ እንስጥ በሚል ተከታታይ Exit Strategy ተዘጋጅቶ ነው ወደ መመሪያ የተቀየረው። ስለዚህ የመመሪያ ዝግጅቱ በተቻለ መጠን አለም አቀፍ ተሞክሮ፣ አህጉር አቀፍ ተሞክሮ እና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በማየት ነበር የተዘጋጀው።
ሌላኛው አስፈፃሚ አካል ነው። ይህን መመሪያ የሚያስፈፅም ኮሚቴ አለ። ይህ ኮሚቴ እግር ኳሱ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ከሚሆን በተቻለ መጠን ምርመራውንም ለማስፋት ግኝቶችንም ለማግኘት በሚል ደጋግመን እንደምንገልፀው የፌደራል ፖሊስ፣ ኢንሳ፣ ፀረ ሙስና በሙያው ላይ ልምድ ያላቸው ሌሎች የመንግስታዊ የህግና የኦዲት ተቋማት ጨምሮ ያካተተ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የተፈፃሚነቱ ወሰን በተመለከተ በክለቦች፣ በክለብ አመራሮች እና በክለብ አባላት፣ በተጫዋቾችና አሰልጣኝ ላይ፣ በተመዘገቡ ቡድን አባላት ላይ ተፈጻሚ የሚደረግ መመሪያ ነበረ። በተግባር ስናየው ደግሞ የመጀመሪያው አመት ላይ የነበረው አፈፃፀም ቀላል አልነበረም። ብዙ ቻሌንጆች ነበሩት። ይህንን ማንኛውም ሚዲያ እና ማንኛውም የስፖርቱ ቤተሰብ የሚያውቀው ነው።
በተቻለ መጠን ማጣራት ተደርጎ የተቀጡ ክለቦች ነበሩ የተቀጡ ተጫዋቾችም በተመሳሳይ ነበሩና ይህ ግን ቀላል አልነበረም። ኬዞች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይሄዱ ነበረ። በስተመጨረሻ CAS ላይ ሁሉ የደረሱ ጉዳዮች አሉና ዋንጫ የመንጠቅ በወራጆችና በማያወርዱት ክለቦች መካከል ህልውናን መሰረት ያደረገ መንገራገጭን የፈጠረ ነው የመጀመሪያው አመት ላይ።
ሁለተኛው አመት ላይ ደግሞ ባህሪው ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ስለዚህ ከመመሪያው አንቀፆች ላይ በብዛት የመመርመር ስልጣን ወስደን የምንመረምረው ጥቆማና ምስክርነትን መሰረት ባደረገ የአካውንት ፍተሻ ነው የሚደረገው። በሶስተኛ ወገንም ይሁን በሌላ አካል የገባለት ክፍያ አለ ወይ? የሚለውን ምርመራ ነው የምናደርገው። አንቀፆችም የሚጋብዙን ስልጣንም የሰጡን በዚህ ላይ ነውና እሱን ስናደርግ ቆይተን በተገኙ ግኝቶች እንዳልኩት የመጀመሪያው አመት ላይ ቅጣት ተላልፎ ነበረ። እንደዚያም ሆኖ በስተመጨረሻ ያለው ነገር ግን በሚጠበቀው አልነበረም።
በማስረጃ ባይደገፉም በሚመጡት መረጃዎች ነገሮች በዓይነት እንደሆኑ መረጃዎች ይመጣሉ። በዶላር፣ በወርቅ፣ በመኪና፣ በመሬት፣ በተለያዩ ንብረቶች እና በካሽ እንደሚሰጥ መረጃዎች ይመጣሉ። እነዚህን በማስረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋሉ። በዚህ አይነት አከፋፈል እንዳለ ይመጣል እነዚህን ኢንቨስቲጌት ማድረግ ደግሞ አስቸጋሪ ነው። እንኳን እነዚህን አይደለም በመደበኛ የፋይናንስ ስርዓት የሚያልፉትን ራሱ ለመቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ነው።
ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑበት ወቅት ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ በክለብ አሰልጣኞች፣ በክለቦች፣ በክለብ አመራሮች እንደሚገለፀው መመሪያው እየተጣሰ ነው፣ ፍትሃዊ እግር ኳስ ውድድር እያደረግን አይደለም የሚል፣ እንዲሁም ጋዜጠኞችም ጭምር የሚያነሱት ሀሳብ ነውና እነዚህ ሀሳቦች ሲሽከረከሩ ቆይተዋል።
ስለዚህ እንዳይተገበር በርካታ እንቅፋቶች አሉ። ነገር ግን ላወጡት መመሪያ ስብሰባ ላይ አጨብጭበው ላፀደቁት መመሪያ ክለቦች ተገዢ አልነበሩም ማለት ይቻላል። ሁሉንም መፈረጅ ባይቻልም በጉባኤው ላይም እንደሚያነሱት “ተገዢ አልነበርንም ጥፋተኞቹ ክለቦች ነን” ያሉ የክለብ አባላት አሉና በዋናነት ክለቦቻችን ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ለህጉ ተገዢ አልሆኑም። ስለዚህ መመሪያውን ማስቀጠል እጅግ አስቸጋሪ ነበር። እንደ አጠቃላይ ጠንካራ የኦዲት ስርዓት በሌለበት ለማክበር ተገዢነቱ በሌለበት ሁኔታ አስቸጋሪነቱን ያጎላዋል። በመጨረሻ ከባለቤትነት ጋር የሚነሱ ሀሳቦችን መልስ ለመስጠት ይህ መመሪያን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያዘጋጀው እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አንድ መመሪያ ተደርጎ የተወሰደ ፣ በፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተፈርሞበት ለፊፋ እና ካፍ የተላከ ሰነድ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ሀሳቦች እየተሰጡ ነው ፤ አክሲዮን ማኅበሩ፣ ፌዴሬሽኑ፣ ክለቦች ወይስ ማን ነው ይህንን መመሪያ ለማስተግበር ዳተኝነት ያሳየው? በማኅበሩስ በኩል መመሪያውን ለማስተግበር የነበረው ቁርጠኝነት ምን ይመስል ነበር ?
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መመሪያው መነሳት ተከትሎ የተለያዩ ሀሳቦች እየተሰጡ ነው። ውሳኔው ላይ ብቻ ሳይሆን ሂደቱም ላይ ሲሰጡ ቆይተዋል። እኔም በግሌ ሌሎችም የተቋሙ ሀላፊዎች ምላሽ ስንሰጥ ቆይተናል። አጠቃላይ ግን ይህ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ ለሀገሪቱ እግር ኳስ በመቆርቆር ‘አማራጩ ይህ ነበር’ በሚል ‘እንዲህ ቢሆንስ’ የሚል በጎ አስተያየት የሰጡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። እነዚህን አስተያየት እናከብራለን። በተቃራኒው ደግሞ አሰራርን መመሪያን እና ሂደትን ባለመረዳት ደግሞ የተሰጡ አስተያየቶች አሉ። እነዚህን ምንም ማድረግ አንችልም ከግል ፍላጎት ናቸው ብለን ነው የምንይዘው።
እንደ አጠቃላይ ግን መመሪያውን ለማስፈጸም የተፈፃሚነት ወሰኑ በክለቦች ላይ የተንጠላጠለ ነው። ክለቦች ብሎም የክለብ አባላት ላይ ተፈፃሚ የሚሆን መመሪያ ነውና ይህን አለማክበር የታየው አጠቃላይ ክለቦች ላይ ነው። ላወጡት መመሪያ በጉባኤዎች ላይ አጨብጭበው በሙሉ ድምጽ የሚያፀድቁትን መመሪያ ተግባር ላይ ደግሞ ተመሳሳይ የሆነ ትብብር እንዳላሳዩ አክሲዮን ማህበሩ ገምግሟል። የጉባኤ አባላትም በነበሩ መድረኮች ላይ ያረጋገጡት እርስ በእርስ የተወቃቀሱበት ነው።
አክሲዮን ማህበሩ በኩል በተመለከተ በተደጋጋሚ የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅም ጭምር፣ የቦርድም አመራሮች በተለይም የአክሲዮኑ ስራ አስኪያጅ “ካልተገበራችሁት ይነሳ በሉ፤ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና አስፈላጊውን ካፒታል እዚህ ላይ ኢንቨስት እያደረግን ተጣባቂ ውጤት ካልመጣ እየተሸዋወድን መቀጠል አንችልም” ብለው በተደጋጋሚ መድረኮች ላይ ሌሎችም የጉባኤ ተሳታፊ አባላት ሊመስክሩበት የሚችሉበት ከዚህ በፊት ተነስቷል። የአፈጻጸም ቸልተኝነቱም ተግባር ላይም የታየው በክለቦች ላይ ነው ብዬ ነው የምወስደው። ሁሉንም ክለቦች መወቀስ ባይቻልም በማስረጃ ባይመጣም መረጃዎች የሚያሳዩት ግን ክለቦች ወጥ በሆነ መንገድ እኩል እየተገበሩት እንዳልሆነ ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስፈላጊውን ትብብር አድርጓል። መመሪያው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ተፈርሞበት የወጣ ነው። ይግባኝ የሚቀርበው በተመሳሳይ ለይግባኝ ኮሚቴ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስፈላጊውን ትብብር አድርጓል። አባላትንም ልኳል፣ በኮሚቴው ላይ የዲስፕሊን ኮሚቴ በአባልነት ሆኖ ኮሚቴ ውስጥ እየሰራ ይገኛልና አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር አድርጓል። ግን ተፈፃሚ ካልሆነ፣ የሚያጠራጥር ነገር ሁሉ ካለ ግን የፍትሃዊ እግር ኳስ ውድድሩ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ይታወቃል። በተደጋጋሚ እኛ ስንጠየቅ የነበረው በተለይም በባለሙያዎች፣ በአሰልጣኞች፣ በጋዜጠኞች እና በሌሎችም እንዲህ አይነት የተፈፃሚነት ችግር ካለ፣ የመተግበር ችግር ካለ ፍትሃዊ እግር ኳስ ውድድር ለማድረግ አስቸጋሪነቱ ግልፅ ነውና እነዚህ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ውድድርን ፍትሃዊነት አስጠብቄአለሁ ማለት ያቸግራልና እነዚህ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት መመሪያው ሲፀድቅ በሙሉ ድምፅ ከሁለት ዓመት በኋላ መመሪያው እንዲነሳ በአብላጫ ድምፅ የወሰኑት ክለቦች በነፃ ገበያ ውድድራቸውን ማድረጋቸው ለሊጉ አልፎም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ምን አይነት ጥቅም እና ጉዳት ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ ?
መመሪያው ስወጣ በዋናነት ታሳቢ የሚያደርገው ገንዘብ ተገቢው ቦታ ላይ ይዋል ነው። በአጠቃላይ ክለቦች 80 እና 90% በጀታቸውን ለተጫዋች እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ደመወዝ ያውላል ቀሪ ስራዎች ደግሞ እየተሰሩ አይደሉም ነው፤ የታዳጊ ልማት ላይ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ግን ምንም በሚያስብል ደረጃ ስራዎች አልተሰሩም። በአስደንጋጭ ሁኔታ የተደራጀ ቢሮ የሌላቸው ክለቦች አሉ፤ ተገቢ ባለሙያ እየቀጠሩ አይደለም ፤ አንድ ባለሙያ ብቻ የሚገኝበት ክለብ ሁላ እንዳለ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። ይሄንን ሁኔታ ካስረዳ በኋላ በቂ ጥናትም ከተደረገ በኋላ አክሲዮን ማህበሩ እንደተባለው በሙሉ ድምፅ ነው የፀደቀው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደርስለታልን በሚል ማለት ነው። ተግባራዊነት ላይ ግን ምንም የታየ ለውጥ የለም ማለት ይቻላል። ያከበሩ ክለቦች አሉ፤ ላከበሩ ክለቦች ደግሞ ውለታውን የሚከፍለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ነው፤ ያላከበሩ ክለቦች ደግሞ ልጠይቃተው የምችለው ያላዋሉት የበደሉት ሴክተር ነው።’
እንደ አጠቃላይ መመሪያው ባለመፈፀሙ ወይንም በቀጣይ አመት ይሄ መመሪያ ባለመኖሩ በዋነነት የሚጎዳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ያለው ሌሎች መፍትሔ የሚሹ ችግሮቻችን ናቸው። የታዳጊ ቡድኖች የሉንም በተደራጀ ሁኔታ ሌሰን ፕላን ስልጠናቸውን እየወሰዱ አይደለም፤ ቡድኖቹ የተሟሉ አይደሉም፤ በተመሳሳይ አወዳዳሪው አካል በሚያዘጋጀው የልምምድ ሜዳ ነው ክለቦች ልምምድ የሚያደርጉት የመጫወቻ ሜዳ ጭራሽ የማይታሰብ ሆኗል፤ አንድም ክለብ የውድድር ሜዳ ባለቤት አይደለም በተለይ የሊጉን ውድድር ባደረግንባቸው አመታት ላይ የአክሲዮን ማህበሩ በሚያዘጋጀው ሜዳ ነውና እነዚህ ኢንፍራስትራክቸሮች ላይ መዋል ያለበት ገንዘብ እንዳይውል በመሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አጠቃላይ ውድድሩ ይጎዳል። ከዛ ውጭ ግን የተለየ የሚገኝ ጥቅም የለም ምናልባትም ጥቅም ሳይሆን እኛ የምንለው እዚህ ስራ ላይ በሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማይሆን ስራ ላይ ጊዜን ጉልበትን ከማዋል ሌሎች ነገሮች ላይ አክሲዮን ማህበሩ ቀላል የማይባል ገንዘብ ጊዜና ጉልበት ነው የወጣበት ይሄንን መመሪያ ለማስተግበር እና ይሄንን ጊዜ እና ጉልበት በሌሎች ችግሮች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የምናገኘው ኃይል ካልሆነ በስተቀር እኛ የምናገኘው የተለየ ጥቅም የለም። የእኛ ዋና ጥቅማችን መመሪያው ተከብሮ መመሪያው ቀጥሎ ብቻ ሳይሆን በመተግበሩ የሚገኙ እግር ኳሳዊ ትረፋቶችን ነበር ተስፋ የምናደርገው።
የአክሲዮን ማኅበሩ ጉባኤዎች ለሚዲያ ዝግ የሚሆኑበት ሂደት ከምን መነሻነት እንደሆነ ብታስረዳን?
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በንግድ ህግ የተቋቋመ የቢዝነስ ተቋም እንደመሆነ መጠን አጠቃላይ አሰራሮቹም በዚህ የተቃኙ ናቸው። ስለዚህ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ሚዲያን እንድንጠራ የሚያስገድድ ህግ የለም ፤ ነገር ግን እንደአስፈላጊነቱ ውሳኔዎች ከተሰጡ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል፤ ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም አካል ለጠየቀው ጥያቄ በውሳኔዎቹ ላይ ሁሉም የስራ ሀላፊ በተባባሪነት ማንኛውም ቃለመጠየቅም ይሁን መረጃዎችን ልሰጥ ይችላል። ምንም እንኳን ሚዲያዎች ባይገኙም የኛ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ይሄንን ቢደግፍም ጉባኤው ግን በውል እና በሰነዶች ማረጋገጫ ባለሙያዎች ተገኝተው ትክክለኛ ተሳታፊዎች ናቸው ወይ የተሳተፉት የሚለውን መረጃ ይዘውበት የሚሄዱት እያንዳንዱ ጉባኤ ደግሞ በፎቶ ብቻ ሳይሆን በቪዲዮ መረጃ እየተቀረፀ የሚቀመጥ ጠቅላላ ጉባኤ ነው።
እንደእግር ኳሱ ደግሞ ካየነው ከንግዱ ጎን ለጎን በሁሉም ጉባኤዎች ላይ አስፈላጊ የተባሉ በተለየም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የበላይ ሀላፊዎች ይገኛሉ። አንዳንዴ ከበላይ ሀላፊዎች በተጨማሪ ኮሚቴዎች እና ዲፓርትመንቶችን የሚመሩ አካላትም እየተገኙ እነዚህ ጉባኤ ላይ ሀሳብ ይሰጣሉ። ከዳኝነት ጋር፣ ከክለብ ላይሰንሲንግ ጋር በተገናኘ፣ ከዲስፒሊን ኮሚቴ እንዲሁም ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የዲፓርትመንቶቹ ሀላፊዎች ብሎም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተቋቋሙ ኮሚቴዎቹ ይገኛሉ። ከእዛ ውጪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ በተለያየ መድረክ ስመቻቸው ሁለቱም ባልተመቸ ሁኔታ ከሁለቱ አንዱ እየተገኙ በጉባኤው ላይ ሀሳብ የሚሰጥበት፤ ሀሳብ በነፃነት የሚሻራሸርበት መድረክ ነው፤ ያንን እየተገበርን ቆይተናል በቀጣይ የምንተግብረው ይሄንን ይሆናል ማለት ነው።
በስተመጨረሻ በተባለው ጊዜ እና ሰዓት ጉባኤዎቻችን ስንት ጉባኤ ተፈቅዶልናል ስንቱ በመደበኛ፣ ስንቱ በአስቸኳይ የሚለው በተለይ ደንቦቻችን ላይ በግልፅ ስለተቀመጠ ያንን በማከለ መልኩ ነው የምንሄደው። ምናልባት ግን እንደ ሀሳብ በግል ከዚህ በፊት የነበሩ ጉባኤዎቻችን ላይ ሚዲያ ሲገኙ ነበረ ወይንም ሌሎች የስብሰባ መድረኮች ክለቦችን ተሳታፊ ያደረጉት ላይ እነዚህ ላይ ግን የሙያ ምግባሩ ይፈቅዳል ብዬ ባላምንም እከሌ ይሄንን አለ፣ እከሌ ይሄንን አለ የሚል የሀሳቡ ባለቤትን የሀሳብ ነፃነት በሚገድብ መንገድ ያሉ የዘገባ አሰራሮች ቢታረሙ ብዬ እኔ በግሌ ወስዳለሁ፤ አጠቃላይ ሙሉ ሂደቱን ልዘግብ የተገኘ ባለሙያ ስብሰባው እየተካሄደ ባለበት አካሄድ ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እነዚህ ፅሑፎች በሚፃፉበት ወቅት ላይ አጠቃላይ ውሳኔዎች ላይ አሰራርም ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፣ ባለሙያውንም አጠቃላይ ጫና ውስጥም ሊከተው ይችላል እና እኔ በግሌ እነዚህን አሰራር አልደግፍም።
ይህ የክፍያ መመሪያ አሁን ላይ ቢነሳም በቀጣይ ምን አይነት ነገሮች ይፈጠራሉ ብለህ ታስባለህ መረን የለቀቀውን የፋይናንስ አጠቃቀም ለመቆጣጠር?
ይሄ መመሪያ በ2019 አልተተገበረም ማለት አጠቃላይ መመሪያ አልባ ሆነን እንቀጥላለን ወይንም የፋይናንስ ስርዓቱ ምንም መፍትሔ አያገኝም የሚል የመጨረሻ ድምዳሜ የለኝም። በቀጣይ በተሻሉ አማራጮች እና በተሻሉ አሰራሮች ለመስራት እድል ሊፈጥርልንም ይችላል። ቢተገበር የሚያመጣው ትሩፋት እንዳለ ሆኖ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊነቱ ባልተረጋገጠበት ከሚቀጥል ግን በተሻለ አማራጭ መምጣቱ ደግሞ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ። በቀጣይ እንግዲህ ክለቦቻችን በክለብ ቁመና ልክ ላይ ሲገኙ ነው ሁሉም ሊተገበር የሚችለው እና ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ይሄንን ተግባራዊ ሲያደርጉ ከክለብ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያቸው ጋር አንድ አካል አድርገው የሚተገብሩ አሉ።
እንደ አፍሪካ ሀገራት መሠረታዊ በአውሮፓ በፋይናንሻል ፌር ፕሌይ ህግ ሙሉ ወጭን ገቢንም በሚቆጣጠር ህግ ሙሉ በሙሉ እንሂድ ማለት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ቁጥጥሩንም ሊያከብደው ይችላል እና ክለቦቻችን እንደ ክለብ ተደራጅተው ተገቢ ባለሙያዎች፣ አስተዳዳራዊ መስፈርቶቻቸውን ያሟሉ፣ የህግ መስፈርቶቻቸውን ያሟሉ፣ አምስቱንም የክለብ ላይንስ የሚያስቀምጣቸውን መስፈርቶች ያሟሉ ሲሆኑ አንደኛው መስፈርት ፋይናንሻል ነውና በዚህም ላይ ጠንካራ ኦዲት የሚደረጉበት በውጪ ኦዲተር ኦዲት የሚደረጉ ከሆነ አጠቃላይ እነዚህን መቆጣጠር ይቻላል ፤ እንዲሁም ጠንካራ የዝውውር መመሪያ እና አተገባበር ሊኖረን ይገባል። የሚፈጠሩ ግርግሮችን ሊቀንስ የሚችል የተጫዋቹን መብት ሊያስጠብቅ እንዲሁም የክለብንም መብት ሊያስጠብቅ የሚችል መመሪያዎች ያሉንን ማሻሻል በተለይ በእጅ ላይ ያሉትን ማሻሻል ሊኖር ይችላል። እነዚህን እየሞከርን ክለቦቻችን እንደክለብ በክለብ ቁመና ላይ ሲገኙ ሁሉም ነገር መፍትሔ ያገኛል ብዬ አስባለሁ።

