በቅርቡ የኢትዮጵያ መድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው በተሾሙት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ እና በኢትዮጵያ መድን ዙርያ ስለ ተፈጠረው ዝርዝር ጉዳይ

ከአራት ዓመት የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ኢትዮጵያ መድን ቆይታ በኋላ ለ2019 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወቃል። ክለቡ እስከሁን ወደ ዝውውሩ በይፋ ሳይገባ በቡድን ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት በማድረግ ላይ ቢቆይም ባለፉት ጥቂት ቀናት ግን በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ እና በኢትዮጵያ መድን መካከል ንፋስ ሳይገባ እንዳልቀረ ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የክለቡ የበላይ አካልና የቦርድ አባላት ጨምሮ ፅሕፈት ቤት፣ ቴክኒካል ዳሬክተር እና አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በዝውውር እንዲሁም ከ2019 ውድድር ዓመት ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት እና አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ ስራ ለመግባት በትናንትናው ዕለት ቀጠሮ ይዘው ነበር። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት በክለቡ በኩል ያሉ የሚመለከታቸው ሀላፊዎች የስብሰባውን ሰዓት ጠብቀው ቢገኙም አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ግን መገኘት አልቻሉም።
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ክለቡ አመራሮችም ዛሬ አሰልጣኙን በስልክ እያዋሯቸውን እንደሆነ ሰምተናል። ይህንን ዜና እስካናጠናከርበት ሰዓት ድረስም በሁለቱም ወገኖች ያለው ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማወቅ አልቻልንም። ሶከር ኢትዮጵያ ከታማኝ ምንጮቻችን እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ግን አሰልጣኝ ደጉ በአንዳንድ ጉዳዮች ዙርያ ደስተኛ እንዳልሆኑ እና ከክለቡ ጋር የሚቀጥሉበት ዕድል ጠበብ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ በሁለቱም ወገኖች ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን ተከታትላ የምትመለስ ይሆናል።

