የኢዮብ ዓለማየሁ ጉዳይ እልባት አግኝቷል

የኢዮብ ዓለማየሁ ጉዳይ እልባት አግኝቷል

ውዝግብ ፈጥሮ የነበረው የኢዮብ ዓለማየሁ ጉዳይ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።

​የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በተጫዋች እዮብ አለማየሁ እና በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ መካከል በተፈጠረው የቅድመ ውል ውዝግብ ላይ ምርመራ አከናውኖ የመጨረሻ ውሳኔውን ማሳወቁን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። በዚህም​ እዮብ አለማየሁ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር በቃል ደረጃ ተነጋግሮ የወሰደውን ቅድመ ክፍያ ለመመለስና ውል ላለመፈረም ለፌዴሬሽኑ አቤቱታ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ኮሚቴው የቀረቡትን ሰነዶች መርምሮ ውሉ ህጋዊና አስገዳጅ መሆኑን አረጋግጧል።

​የዲሲፕሊን ኮሚቴው ባሳለፈው ውሳኔም “በተጫዋቹና በክለቡ መካከል ሐምሌ 30 ቀን 2018 የተደረገው ቅድመ ውል (Pre-Contract) የፊፋ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደንቦችን ያሟላ በመሆኑ ህጋዊና አስገዳጅ ነው ፤ በመሆኑም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተጫዋቹ ህጋዊ ባለቤት ነው” ብሏል።

​ፌዴሬሽኑ ባወጣው የውሳኔ ደብዳቤ ላይ ወልዋሎ የተጫዋቹ ህጋዊ ባለቤት በመሆኑ ተጫዋቹ በአካል ቀርቦ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ዋናውን ውል መፈረም እንዳለበት ተመላክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቹ ይህንን ውሳኔ ተላልፎ ከሦስተኛ ክለብ ጋር ቅድመ ውል ወይም ዋና ውል ቢፈርምና ክለቡ በሚያቀርበው አቤቱታ መሠረት በውል ማፍረስ (Breach of Contract) ደንብ መሠረት ተጫዋቹና ውል ያደረገው ክለብ ላይ ጥብቅ የእገዳና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቅድመ ክፍያን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፋይናንስ መመሪያ ቁጥር 1/2016 አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 5.2.4 “ማንኛውም ክለብ ለተጫዋቾቹ የደሞዝ እና የፈርማ ክፍያ በቅድሚያ መክፈል አይችልም” የሚል በመሆኑ ሁለቱም ወገኖች ይህንን መመሪያ በመጣሳቸው ጉዳዩ ተጣርቶ አስፈላጊው ውሳኔ እንዲሰጥበት ሰነዶቹ ለፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ እንዲላኩ ተወስኗል።