ዋልያው ከ64 ዓመታት በፊት የአህጉሪቱ ቻምፒዮን በነበረበት ወቅት በዳካር ከተማ ያፈሰውን ድል ለመድገም ይፋለማል።

በቅድመ ማጣሪያ ውድድር ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን አሸንፈው ወደ 2027 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ውድድር የበቁት በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ የሚሰለጥኑት ዋልያዎቹ ከቀናት በፊት ባደረጉት የውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ በሱዳን አንድ ለባዶ መሸነፋቸው ይታወሳል። መስከረም 19 : 10 ሰዓት በባህርዳር ለሚደረገው የምድብ ማጣሪያው ሁለተኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀደም ብሎ በስፍራው የደረሰ ሲሆን የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ከሞዛምቢክ መዲና ማፑቶ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ጉዞ ጀምሯል።
ከቀናት በፊት ባደረስናችሁ መረጃ መሰረት በቅርቡ በተከናወነው የአፍሪካ ከ 17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከ ሞሮኮ ጋር ያደረገችውን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመሩት ካሜሩናዊው ዋና ዳኛ ዊሊ ስቴፋን ንጋህ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የሚመሩ ሲሆን ቪንሰንት ንጊማዶህ እና ቦዞይ ኦሪያ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም አንድሬ ኦነሲሜ አራተኛ ዳኛ ሆነው ጨዋታውን ይመሩታል።
ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል በታሪካቸው አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አንድ የወዳጅነት ፤ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና አንድ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ጨዋታዎች አድርገዋል። በፍልሚያዎቹ የቴራንጋ አናብስት ሦስት ጊዜ ድል ሲያደርጉ ዋልያዎቹ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። ከ 64 ዓመትና 10 ወራት በፊት በዕለተ ማክሰኞ ሕዳር 12 1954 በተደረገ ጨዋታ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን በተቀሩት አራት የነጥብ ጨዋታዎች ግን ሴኔጋል ባለ ድል ሆናለች። በአራቱ ፍልሚያዎች በድምር 15 ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ኢትዮጵያ 4 ሴኔጋል ደግሞ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።
የሁለቱ ሀገራት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ የአህጉረ አፍሪካ እግር ኳስ ቁንጮ በነበረችበት እና የአፍሪካ ዋንጫን ባሸነፈችበት ማግስት የተደረገ ከጋና አፍሪካ ዋንጫ በፊት የተደረገ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሲሆን የመጨረሻ ጨዋታቸው ደግሞ ከ29 ዓመታት በፊት እሁድ ሰኔ 15: 1989 የተደረገና በሴኔጋል 3 ለ 0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ነበር።
በመጀመሪው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ውድድር ጨዋታ ድል ማድረግ ያልቻሉት ሁለቱ ሀገራት ከቀናት በኋላ በባህርዳር ከተማ በሚደረገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ከጉዳት ነፃ የሆነውን ስብስባቸውን ይዘው ለጨዋታው ይቀርባሉ።

