ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ያገለለው የሲዳማ ቡና ተጫዋች ዳግም ጥሪ ደረሰው

ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ያገለለው የሲዳማ ቡና ተጫዋች ዳግም ጥሪ ደረሰው

ከሳምንታት በፊት ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ያገለለው ዩጋንዳዊው የሲዳማ ቡና ተጫዋች በደጋፊዎቹ ፊት በክብር እንዲሸኝ ጥሪ ቀረበለት።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የታንዛኒያውን ሲንጊዳ ብላክ ስታርስን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ዩጋንዳዊው አማካይ ካሊድ አውቾ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ከሳምንታት በፊት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።

ለ13 ዓመታት ሀገሩን ያገለገለው ካሊድ አውቾ 77 ጨዋታዎችን ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ያደረገ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በይፋ ከቡድኑ ራሱን ካገለለ በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ፖል ፑት በቀጣይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቦትስዋና ጋር ላለባቸው ፍልሚያ 30 ተጫዋቾችን ሲጠሩ አምበሉን በዝርዝሩ ውስጥ አካተዋል።

የክሬኖቹ አለቃ ፖል ፑት የተጫዋቾቹን ዝርዝር ይፋ ሲያደርጉ እንደገለፁት ተጫዋቹ ራሱን እንዳገለለ ከገለፀ በኋላ አግኝተው እንዳዋሩትና በደጋፊዎቹ እና ጓደኞቹ ፊት በክብር አሸኛነት እንዲደረግለት አስበው ጥሪውን እንዳደረሱት አመላክተው እርሱም በሀሳቡ እንደተስማማ ገልፀዋል።

በሲዳማ ቡና የሚገኘው ተጫዋቹ ኖቬምበር 14 ዩጋንዳ ከቦትስዋና ጋር በሆሚያ ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ በክብር የሚሸኝ ይሆናል።