ያለ ዋና አሠልጣኙ መሳይ ተፈሪ የግብ ናዳ ሀላባ ከተማ ላይ ያወረደው ወላይታ ድቻ የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የሶከር ኢትዮጵያ ኤዲቶሪያል ሌላኛው ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አብዛኛዎቹ መርሐ-ግብሮች በጠበበ የውጤት ልዩነት፣ በጥንቃቄ አዘል አቀራረቦች እንዲሁም አንዳንዴ በሚስተዋል የግብ ድርቅ የሚጠናቀቁ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ትንተና የሚፈልግ ቢሆንም ከትናንት በስትያ ከዚህ በተቃራኒ የተመለከትነው የወላይታ ድቻ እና የሀላባ ከተማ ጨዋታ ግን የተለመደውን የሊጉ ገጽታ ያስረሳ የጎል ፌሽታ የታየበት እንዲሁም በሊጉ ታሪክ ለየት ያለ ቦታ የሚሰጠው ነበር።
ከውጤቱ መስፋት ባሻገር ጨዋታውን ልዩ እና አነጋጋሪ የሚያደርገው ዋናው ጉዳይ ወላይታ ድቻ ያለ ዋና አሠልጣኙ መሳይ ተፈሪ (በቅጣት ምክንያት) በከፍተኛ የቁጭት መንፈስ ወደ ሜዳ ገብቶ ይህን ታሪካዊ ድል ማስመዝገቡ ነው። ይህንን ክስተት ከዘመናዊ እግር ኳስ የስነ-ልቦና መነፅር፣ የቡድን አብሮነት እና ከሜዳ ውጪ ባሉ ሌሎች ምክንያቶች ተነሳስቶ ጨዋታን ከማድረግ አንፃር በስፋት ስንመረምረው የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስቀመጥ ወደድን።
አንደኛው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ የስነ-ልቦና ጫናን ወደ አዎንታዊ የነጻነት ስሜት ከመለወጥ አንፃር የታየው የድቻ ጠንካራ ጎን ነው። በእግር ኳስ አሠልጣኝ የቡድኑ አንጎል፣ መሪ እንዲሁም የታክቲክ ቀያሽ እና ዘዋሪ ነው። ዋናው አሠልጣኝ በቅጣት ምክንያት በሜዳ ዳር ተገኝቶ ቡድኑን መምራት ሳይችል ሲቀር በቡድኑ ላይ የስነ-ልቦና ጫና ወይም የመሪነት ክፍተት ይፈጠራል ተብሎ ይሰጋል። ይሁን እንጂ በሰለጠነው የእግርኳስ ዓለም እንደሚታየው ይህ ድንገተኛ ክፍተት በተቃራኒው ተጫዋቾች ራሳቸውን እንዲችሉ እና የላቀ የጋራ ኃላፊነት እንዲወስዱ ከፍተኛ ግፊት እንደሚፈጥር ነው። በሌሎች ሀገር ሊጎች አሠልጣኞች ከሜዳው ጠርዝ ተገልለው ሲቀመጡ ተጫዋቾች “ለአሠልጣኛችን እና ለራሳችን ክብር ስንል” በሚል ተጨማሪ ሩጫ እና ትኩረት አሳይተው ድል የሚያስመዘግቡባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ወላይታ ድቻዎችም ያለ ዋና አሠልጣኛቸው ወደ ሜዳ ሲገቡ የተሰማቸው ስሜት ልክ ይህንን የቁጭት እና የትብብር መንፈስ የሚጋራ ሲሆን ሜዳ ላይ የነበረው ነፃነት እና የጋራ መረዳዳት ቡድኑን ወደር የለሽ የጥቃት ብቃት እንዲደርስ አድርጎታል።
ሌላኛው ጉዳይ ለደጋፊና ለክብር የተደረገ የሞራል ተጋድሎን በተመለከተ በጦና ንቦቹ ዘንድ የታየው መነሳሳት ነው። አንድ ቡድን ከጠበቁት ውጪ ከሆነ ዝቅ ያለ አፈፃፀም እና ሽንፈት መልስ ሲመጣ የሚኖረው ምላሽ የቡድኑን የስነ-ልቦና ጥንካሬ ይለካል። ወላይታ ድቻዎችም ከዚህ ቀደም ከነበሩ ውጤቶች በመነሳት በደጋፊያቸው እና በራሳቸው ላይ የነበረውን “ዕዳ” ለመክፈል ቆርጠው መነሳታቸው በሜዳ ላይ ከነበረው ከፍተኛ የአጨዋወት ፍጥነት በግልጽ ተስተውሏል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የዲቻ ደጋፊዎች ለክለባቸው ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው። ተጫዋቾች ለታመኑት ደጋፊዎቻቸው፣ ለራሳቸው ሙያዊ ክብር እና በቅጣት ለተገለለው አሠልጣኛቸው ሲሉ ያሳዩት ተጋድሎም በዚህ አስተያይ እጅግ የሚደነቅ ነው። በሊጉ 6 ጎል ማስቆጠር ቀላል አይደለም ፤ ይህ ድል የሚያሳየው ቡድኑ እስከ መጨረሻው ሰከንድ ድረስ ተጋጣሚውን በማጥቃት ደጋፊውን ለማስደሰት የነበረውን ከፍተኛ ጥማት እንዳሳየ መመልከት ይቻላል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ 6 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ግቦች የሚቆጠሩት እጅግ አልፎ አልፎ ነው። አብዛኛዎቹ ክለቦች ጥንቃቄ ምርጫ ባደረገ ቅድሚያ ለመከላከል በሚሰጥ አጨዋወት እና ኳስን ጠብቆ የመጫወት አዝማሚያ ስለሚኖራቸው ውጤቶች ብዙውን ጊዜ በጠበበ ልዩነት ይጠናቀቃሉ። ይህንን ያህል ሰፊ ውጤት መመዝገቡ የሀላባ ከተማን የተከላካይ መስመር ድክመት ቢያጋልጠውም ከሁሉ በላይ ግን የወላይታ ድቻን የጥቃት መስመር ቅንጅት በድምቀት ያሳየ ነው። ለዚህም ማሳያ እጅግ ከረጅም ጊዜ በኋላ ሊጉ ሶስታ ወይም ሀትሪክ እንዲመዘገብበት ሆኗል። አጥቂዎች በራስ መተማመን ሲሞሉ፣ የሜዳ ላይ ቅብብሎቻቸው ፈጣን ሲሆኑ እና ኳሶች በፈጣን ሽግግር ወደ ሳጥን ሲደርሱ ምን ያህል ገዳይ መሆን እንደሚችሉ ያስተማረ ህያው ማሳያ ነው።
በአጠቃላይ የወላይታ ድቻ የ6ለ0 ድል ከቀላል የሦስት ነጥብ ጨዋታ በላይ የቁጭት፣ የቡድን አብሮነት እና የሞራል ከፍታ ማሳያ ነው። አሠልጣኙ ከሜዳ ውጪ ሆኖ ሳለ ተጫዋቾቹ ያሳዩት ብስለት፣ የዲሲፕሊን ጥንካሬ እና የማሸነፍ ፍላጎት ለሌሎች ክለቦችም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። እግር ኳስ ስሜት፣ አልሸነፍ ባይነት እና እስከ መጨረሻው መዋጋት መሆኑን ያስመሰከረ ውብ ምሽት ነበር። ድቻዎችም ይህንን የሞራል ከፍታ እና የጥቃት አቅም ይዘው በቀጣይ መርሐ-ግብሮቻቸው መቀጠል ከቻሉ በሊጉ ውስጥ አስፈሪ ግስጋሴ ማሳየታቸው የማይቀር ነው።

