አሰልጣኝ እያሱ መርሃጽድቅ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ መልዕክታቸውን ልከዋል

አሰልጣኝ እያሱ መርሃጽድቅ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ መልዕክታቸውን ልከዋል

👉”የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችና የቡድን አባላት ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እየጠየቅኩ …”

👉 “የተጋጣሚ ቡድን ያስቆጠረውን ጎል የማንቋሸሽ ሀሳብም ሆነ ስነ ልቦና የለኝም፤ የአሰልጣኝነት ስነ ምግባርም አይፈቅድልኝም።

አሰልጣኝ ዶ/ር እያሱ መርሃጽድቅ

ትናንት በተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሸገር ከተማ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኝ እያሱ መርሃጽድቅ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ መልዕክታቸውን ልከዋል።

“እኔ ድሮ እንደዚህ አይነት ጎል ሲገባ የማውቀው የወረዳ ፤ የቀበሌ ጨዋታ ላይ ነው። ግብ ጠባቂው ይጠልዛል ሄዶ አጥቂው ያገባል።” በማለት የሰጡት አስተያየትን መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። አሰልጣኙም በወቅቱ ለማለት የፈለጉትን ምን እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ የላኩትን መልዕክት እንደወረደ አቅርበነዋል።

“ትናንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ላይ በድህረ ግጥሚያ ወቅት በሰጠሁት ቃለ መጠይቅ ማብራሪያ የክለቡን ደጋፊዎች ማሳዘኑን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለመረዳት ሞክሪያለሁ። ይሁንና በወቅቱ ለመናገር የሞከርኩት በቡድኔ ላይ የተቆጠረው የመጀመሪያው ጎል ከራሴ የተከላካይ እንቅስቃሴ ስህተት የመጣ መሆኑን ለመግለጽ ነው።

የእግር ኳስ የመጨረሻ ዓላማ ጎል መሆኑንና በማንኛውም ሁኔታ ማስቆጠር የተጫዋቾች ሀላፊነት መሆኑን እረዳለሁ፤ በየትኛውም የአሰልጣኝነት መስፈርት የተጋጣሚ ቡድን ያስቆጠረውን ጎል የማንቋሸሽ ሀሳብም ሆነ ስነልቦና የለኝም፤ የአሰልጣኝነት ስነ ምግባርም አይፈቅድልኝም። ስለሆነም የታላቁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችና የቡድን አባላት ለተፈጠረው የመረዳት ስህተት ይቅርታ እየጠየቅሁ፣ የተላለፈው አስተያየት ሙሉ ለሙሉ የራሴን ክለብ (ሸገር ሲቲን) የሚመለከት መሆኑን እንዲረዱልኝ በዚህ አጋጣሚ እጠይቃለሁ”