ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 18 | አስታራቂው መሳይ ሰለሞን ከ501 ቀናት በኋላ ሊጉን ከሀትሪክ ጋር አስታርቋል

ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 18 | አስታራቂው መሳይ ሰለሞን ከ501 ቀናት በኋላ ሊጉን ከሀትሪክ ጋር አስታርቋል

ከመሳይ ሰለሞን ሀትሪክ በፊት በሊጉ በ43 የጨዋታ ሳምንታት ውስጥ አንድም ተጫዋች ሀትሪክ ያለመስራቱ ጉዳይ እና የማጥቃት አቀራረብ ውስንነቱ ሌላኛው በሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች የምንመለከተው ጉዳይ ነው።

ወላይታ ድቻ አዲስ አዳጊውን ሃለባ ከተማ ስድስት ለባዶ በረመረበት ጨዋታ ላይ የጦና ንቦቹ አጥቂ መሳይ ሰለሞን ሦስት ግቦችን በማስቆጠር የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከ501 ቀናት በኋላ ከሀትሪክ ጋር አስታርቋል።

ሰኔ 5 በዕለተ ሐሙስ 2017 ዓ/ም በ34ኛው ሳምንት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ወላይታ ድቻን አራት ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ወንድወሰን በለጠ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች በኋላም ከአንድ ዓመት፣ አራት ወራት እና 16 ቀናት በኋላ የተመዘገበ የመጀመሪያው ሀትሪክ ያደርገዋል።

ወግ አጥባቂ እና መከላከል ላይ ያተኮረ አቀራረብ በተጠናወተው፤ ቡድኖች እና አሰልጣኞች ጠንካራ መከላከል ብቻ ዋንጫዎችን ያስገኛል በሚል እምነት በፈጠራ የተሞላ የማጥቃት አጨዋወት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ተከላክሎ ሽንፈትን ማስወገድ እንደ ትልቅ ጀብድ በሚታይበት ሊግ ላይ ሆነህ በርካታ ግቦች ማስቆጠር አደጋች መሆኑ እሙን ቢሆንም በሊጉ በ43 የጨዋታ ሳምንታት ውስጥ አንድም ተጫዋች ሀትሪክ ያለመስራቱ ጉዳይ ሊጋችን ምን ያህል በጎል አስቆጣሪዎች እጥረት እንደተጠቃ ማሳያ ነው።

380 ጨዋታዎች በተደረጉበት እና በራስ ላይ የተመዘገቡ ሳይጨምር 651 ግቦች በተቆጠሩበት የ2018 ውድድር ዓመት ከሁለት ግቦች በላይ ያስቆጠረ ተጫዋች አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.7 ግቦች ብቻ ነበር የተቆጠሩት። እነዚህን ቁጥሮች በግርድፉ ለተመለከተ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ላይ ያለው የአሰልጣኞች የማጥቃት አቀራረብ ውስንነት እና አጥቂዎቻችን ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው።

ግብ ማስቆጠር በዋነኝነት ለአጥቂዎች የተሰጠ ተግባር ቢሆንም ችግሩን በቡድን መነፅር መመልከት ተገቢ ነው። አብዛኞቹ ክለቦች በሚባል ደረጃ የላቀ የፈጠራ አቅም ያለው ተጫዋቾ እጥረት አላቸው፤ ያላቸውም ለተጫዋቹ የሚሰጡት የማጥቃት ነፃነት የተገደበ ነው በጥቅሉ በሊጉ ያሉት አሰልጣኞች ለፈጠራ እና በተጠና የማያቋርጥ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ያላቸው ቦታ አናሳ ነው። ይህም የአገልግሎት ረሃብ ላጠቃቸው እና የሚገኙትን ዕድሎች በመጠቀም ረገድም ጉልህ የአፈፃፀም ክፍተት ካላቸው አጥቂዎቻችን ጋር ተዳምሮ ሊጋችን ከአንድ ዓመት በላይ በሀትሪኮች ድርቅ እንዲመታ እንዲሁም በዓመት 15 ግቦችን ማለፍ ብርቅ አድርጎታል።