ለመቻል እንዲጫወቱ ተወስኖላቸው የነበሩት አብዱልከሪም ወርቁ እና ዓለምብርሃን ይግዛውን በተመለከተ አዲስ ነገር ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ አለምብርሃን ይግዛው እና አብዱልከሪም ወርቁ ከመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ እና ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋር ያደረጉትን የቅድመ ውል ስምምነት ውዝግብ መርምሮ ከሳምንታት በፊት ውሳኔ መስጠቱን ታውቋል። ኮሚቴው የቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎች እና የተጫዋቾቹን ቃል መርምሮ ተጫዋቾቹ ለመቻል እንዲጫወቱ ነገር ግን የ200 ሺ ብር ቅጣት እና ለአራት ወራት ከማንኛውን እግርኳስ እንዲገለሉ ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር አይዘነጋም።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሰረት የመቻል እና የኢትዮጵያ ቡና አመራሮች የክለቡን መልካም ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ተጫዋቾቹን ከቅጣት ለማዳን በመነጋገር አንድ አንድ ተጫዋች እንዲወስዱ መስማማታቸውን በጋራ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ አስገብተዋል። በዚህም ዓለምብርሃን ይግዛው ለመቻል ሲፈርም አብዱልከሪም ወርቁ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ተስማምተዋል።
ከላይ እንደገለፅነው ሁለቱ ክለቦች በጋራ የተስማሙበትን ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ካስገቡ በኋላ ተጫዋቾቹ ለየክለቦቹ እየፈረሙ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም የክለቦቹን እና የተጫዋቾቹን ስምምነት ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ የሚወስነው ውሳኔ ይጠበቃል።

