​የጨዋታ ሪፓርት| ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሁንም ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም 

5ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሲጀመር አዲስ አበባ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከተማን በ09:00 አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቷል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም አጋማሽ የተመልካችን አይን መያዝ ሳይችል የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቶሎ ቶሎ ኳስ በመነጣጠቅ እና በመሀል ሜዳ የተገደቡ ተደጋጋሚ ቅብብሎች የታየበት ነበር፡፡

በዚሁ አሰልቺ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በ17ኛው ደቂቃ ሙሉአለም ጥላሁን ወደ መሀል ያሻገረውን ኳስ የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ጃክሰን ፊጣ ሲመልሰው በአርባምንጭ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች እና በግብጠባቂው አለመግባባት የተገኘችውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ይህች ግብ ለፍፁም ገብረማርያም በሊጉ 2ኛው ናት፡፡

picsart_1481399837042

በዚሁ የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ27ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ማስፋት የሚችሉበትን አጋጣሚ ቢያገኙም ኢብራሂም ፎፋኖ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀር በ44ኛው ደቂቃ አመለ ሚልኪያስ የግሉን ብቃት ተጠቅሞ ያቀበለውን ኳስ ገብረሚካኤል ያዕቆብ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አርባምነጭን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

picsart_1481399875221

በሁለተኛው አጋማሽ 49ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ዳዊት እስጢፋኖስ ምንተስኖት አበራ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ ከዳዊት ቀይ ካርድ በኃላ አርባምንጭ ከተማዎች ያላቸውን የቁጥር ብልጫ ከመጠቀም ይልቅ የአቻ ውጤቱን ለማስጠበቅ መከላከልን በመምረጣቸው ተጨማሪ ግቦች ሳይቆጠሩ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

 

ከጨዋታው በኋላ የተሠጡ አስተያየቶች

picsart_1481400016352

አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ – ኤሌክትሪክ

“በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን የግብ እድሎች ወደ ግብነት መቀየር ባለመቻላችን ነጥብ ተጋርተን ልንወጣ ችለናል፡፡”

“በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋች በቀይ ካርድ ቢወጣብንም የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል፡፡”

“በቡድናችን ላይ ያለው ችግር ብዬ የማስበው በአምስቱም ጨዋታ ላይ የምናገኛቸውን የግብ እድሎች ከመረብ ማገናኘት አለመቻላችን ነው፡፡”

“በኤሌክትሪክ ቤት ስላለመውረድ የሚወራበት ዘመን አብቅቷል፡፡”

picsart_1481399989550

አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ – አርባምንጭ ከተማ

“በሁለተኛው አጋማሽ የነበረንን የቁጥር ብልጫ አለመጠቀማችን ነጥብ ተጋርተን እንድንወጣ አስችሎናል፡፡”

” ተጫዋቾቼ የሰጠኋቸውን ትእዛዝ ባለመፈጸማቸው የቁጥር ብልጫችንን እንዳንጠቀም አድርጎናል፡፡

“ምንም እንኳ ጨዋታውን ማሸነፍ ቢገባንም ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን ያገኘነው አንድ ነጥብ የሚያስከፋ አይደለም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *