ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ 6ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አባላቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ የደጋፊው ማህበር ተወካዮች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በትናንትናው ዕለት በኔክሰስ ሆቴል አካሂዷል።
ክለቡ በጉባዔው ያለፈውን ዓመት አፈፃፀም እና የ2009 ዓ.ም. የስራ ዕቅድ ከመገምገሙ በተጨማሪ የመተዳደሪያ ደንቡን ለማሻሻልም ውይይት አድርጓል።
ተሳታፊዎች ወደስፍራው እስኪመጡ ድረስ የጉባዔው የመጀመሪያ ሰዓት የተራዘመ ሲሆን ከ39 የጠቅላላ ጉባዔው አባላት 25ቱ በመገኘታቸው ጉባዔው እንዲጀመር ሆኗል። የጠቅላላ ጉባዔው ሊቀመንበር አቶ ድንቁ ስለሺ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካሰሙ በኋላ መድረኩን ለክለቡ ቦርድ ፕሬዘዳንት መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ ለቀዋል። መቶአለቃ ፈቃደ ማሞም የክለቡ ቦርድ አመራር አባላት የስራ ሪፖርትን ለጉባዔው አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ እርቁ የክለቡ የቴክኒክ፣ ፋይናንስ፣ የሰው ሃይል እና ጠቅላላ አገልግሎት እንዲሁም የገበያ አስተዳደር እና ማስታወቂያ ክፍሎች በ2008 ዓ.ም. የነበራቸውን የስራ አፈፃፀም ያቀረቡ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል የነበረውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ጠቅሰዋል።
የቀድሞው የክለቡ አሠልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች በነበራቸው ግልፍተኛ ባህሪ፣ ቡድንን የመምራት ችግር፣ ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር በነበራቸው አለመግባባት እና ከሌሎች የአሠልጣኝ ቡድኑ አባላት ጋር በምክክር መስራት ባለመቻላቸው ኮንትራታቸው እንዳይቀጥል መደረጉም በዚህ ወቅት ነበር የተገለፀው።
አቶ በላይ እርቁ አያይዘውም የክለቡን የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ ለጉባዔው ያሰሙ ሲሆን ዋናው የወንዶች ቡድን የፕሪምየር ሊግ እና ጥሎማለፉን እንዲያነሳ፣ የሴቶች ቡድኑ እስከ 5ኛ ደረጃ ድረስ ይዞ ሊጉን እንዲያጠናቅቅ፣ የተስፋ ቡድኑ ከ5 እስከ 7 ተጫዋቾችን ለዋናው ቡድን እንዲመግብ፣ እንዲሁም የ17 ዓመት በታች ቡድኑ በተመሳሳይ ከ5 እስከ 7 ልጆችን ለተስፋ ቡድኑ እንዲያበቃ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቴክኒክ ክፍሉ አዲስ የተጫዋቾች ምልመላ መስፈርት መምሪያን እንዳዘጋጀ እና ይህንንም በአሁኑ ዓመት መጠቀም እንደሚጀምር ተነግሯል።
በ2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የክለብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መጀመር፣ በአቶ አህመድ ያሲን የተዘጋጀ ‘የእግርኳስ ረብሻ እና ነውጠኝነት ማስወገጃ ስትራቴጂ’ ለክለቡ ማህበረሰብ ማስተማር፣ አመታዊ ሩጫ ማዘጋጀት፣ የክለቡን መዝሙሮች ሲዲ እና ማልያዎችን ለገበያ ማቅረብ፣ ከነባር ስፖንሰሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እና አዳዲስ ስፖንሰሮችን ማምጣት የክለቡ የገበያ አስተዳደር እና ማስታወቂያ ክፍል በዕቅዱ የያዛቸው ነጥቦች ናቸው።
ክለቡ በ2008 ዓ.ም. 32 ሚሊዮን ብር ገቢ የነበረው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 28 ሚሊዮን ብሩን ወጪ አድርጓል። በያዝነው ዓመት ደግሞ 43 ሚሊዮን ብር አካባቢ የሚሆን ገንዘብ ለማስገባት እየተሰራ ሲሆን የክለቡ ጠቅላላ ወጪም ወደ 40.5 ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋ ተገምቷል። የቡድኑን ውጤት ከፍ ለማድረግ ሲባል ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ ተጫዋቾች መፈረማቸው፤ የአካል ብቃት፣ የሳይኮሎጂ እና የስነምግብ ባለሞያዎች ተቀጥረው ስራ መጀመራቸው እና የምግብ፣ የሆቴል፣ የትራንፖርት እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ዋጋ መናር ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ወጪው የመጨመሩ ምክንያት ተደርገው ተቀምጠዋል።
የክለቡ የ2008 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት በኦዲት አማካሪው ድርጅት ተወካይ አቶ ኃብተወልድ መንክር ቀርቧል። በመጨረሻም ከ10 ዓመት በላይ በክለቡ አባልነት የቆዩ፣ ክለቡ የተለያየ ችግር ሲያጋጥመው በፋይናንስ እና በሌሎች መንገዶች የደገፉ፣ እንዲሁም በከፍተኛ አመራርነት አገልግለው የስራ ዘመናቸውን ሲጨርሱ ያላቸውን ልምድ ለአዲሱ አመራር እንዲያካፍሉ የሚፈለጉ ግለሰቦች በክብር አባልነት ተመዝግበው ድምፅ ሳይኖራቸው በጠቅላላ ጉባዔው ተሳትፎ እንዲያደርጉ የቀረበው ሃሳብ በስራ አመራር ቦርዱ ማሻሻያ ተደርጎበት በመተዳደሪያ ደንቡ እንዲካተት በመወሰን ጠቅላላ ጉባዔው ውሎውን አጠናቋል።