በ7ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃግብር መከላከያ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከመመራት ተነስቶ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ጎራ ለጊዜውም ቢሆን ተቀላቅሏል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተጀመረው በትላንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት ለተለየው ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመከላከያዎች በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ዳዊት እስጢፋኖስ በ4ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ሞክሮ ግብጠባቂው አቤል የያዘበት እንዲሁም በ6ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም ጥላሁን ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው ኳስ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
በአንፃሩ መከላከያዎች በ14ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ሳሙኤል ሳሊሶ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን አልፎ ለምንይሉ ወንድሙ አቀብሎት ምንይሉ ወደግብ ሲሞክር የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት ኳስ ተጠቃሽ ነበር፡፡
በ19ኛው ደቂቃ ላይ የዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው ኮትዲቯራዊው ኢብራሂም ፎፋና ከአሸናፊ ሽብሩ የተላከለትን ኳስ የግሉን ፍጥነት እና ጉልበት ተጠቅሞ ወደግብነት ቀይሮ ኤሌክትሪኮችን መሪ ማድረግ ቻለ ፤ ይህችም ግብ ለተጫዋቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የግብ አካውንቱን የከፈተባት ሆና ተመዝግባለች፡፡
ከግቧ መቆጠር ሁለት ያክል ደቂቃዎች በኃላ ኤሌክትሪኮች የግብ ልዮነቱን ወደ ሁለት ማስፋት የሚችሉበትን አጋጣሚ ፍፁም ቢያገኝም ከግብ ክልሉ ጠርዝ አካባቢ የሞከረውን ኳስ አቤል ማሞ አድኖበታል፡፡
በተቃራኒው መከላከያዎች በ23ኛው ደቂቃ ላይ በበሀይሉ ግርማ አማካኝነት ከርቀት የሞከሩት ኳስ በአቡ ሱሊይማን በቀላሉ ተይዟል፡፡
በ33ኛው ደቂቃ አለምነህ ግርማ ከግራ መስመር ወደ መሀል ያሻማውን ኳስ ዳዊት እስጢፋኖስ ከተቆጣጠረ በኃላ ወደ ግብ የላካትን ኳስ አቤል ማሞ በአስደናቂ ሆኔታ ሊይዝበት ችሏል፡፡
ከዚህ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በመሀል ሜዳ ላይ እምብዛም ያልተሳኩ ቅብብሎች እና ከተከላካይ በሚጠለዙ ያልተሳኩ ኳሶች ታጅቦ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ 50ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቀኝ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት አዲስ ነጋሽ ገጭቶ የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችው ኳስ በጣም የምታስቆጭ ነበር፡፡
መከላከያዎች በአንፃሩ በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ፈጣን የመስመር አማካዮቻቸውን በመጠቀም ወደ መሀል በሚሻሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በተጨማሪም በ65ኛው ምንይሉ ወንድሙ ከ25 ሜትር ርቀት የሞከራትና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት አጋጣሚ በመከላከያዎች በኩል የምታስቆጭ ነበር፡፡
በ68ኛው ደቂቃ ከሰሞኑ አስገራሚ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የግራ መስመር ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ ከቡድን አጋሮቹ የተቀበለውን ኳስ በግሉ ጥረት ሰብሮ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ከገባ በኃላ በአስደናቂ አጨራረስ ቡድኑን አቻ ማድረግ ቻለ፡፡
ከዚህ ግብ በኃላ የተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት መከላከያዎች የማታ ማታ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ ከርቀት አክርሮ በመምታት በቀድሞ ክለቡ ላይ ባስቆጠራት አስገራሚ ግብ ቡድኑን አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡
ይህ ድል ለመከላከያ በ4 ጨዋታ 3ኛው ሲሆን በሶስተኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰባቸው የ3-0 ሽንፈት በኃላ በተከታታይ ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች
3ቱን አሸንፎ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይቶ በ11 ነጥብ ነገ ከሚጫወቱት የሊጉ መሪዎች ተርታ መሰለፍ ችሏል፡፡
በአንፃሩ ተሸናፊዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግም ከሰባት ሳምንት መርሃግብር አስካሁን ድረስ ምንም ድል ማስመዝገብ ሳይችሉ በአራቱ አቻ ተለያይተው አሁንም በወራጅ ቀጠና እየዳከሩ ይገኛል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ሻለቃ በለጠ ገብረኪዳን – መከላከያ
“ቅድሚያ ባስቆጠሩብን ግብ ብንመራም ተጫዋቾቼ በነበራቸው ፍላጎት እና የአካል ብቃት የተሻሉ ስለነበሩ ከመመራት ተነስተን ልናሸንፍ ችለናል፤ በዚህም ተጫዋቾቼ በዘጠናው ደቂቃ ባሳዮት እንቅስቃሴ ኮርቻለሁ፡፡”
“በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾቼ ኳስን በመቆጣጠር ሆነ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ስለነበሩ ወሳኙን ነጥብ ይዘን ልንወጣ ችለናል፡፡
ብርሃኑ ባዩ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
” ከዕረፍት በፊት እንዳያችሁት በርካታ የጎል እድሎችን መፍጠር ችለናል፡፡ ነገር ግን መጠቀም አልቻልንም ፤ አንድ ለዜሮ እየመራን ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ነበረብን ፤ ብቻ ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ አልተሳካልንም ፤ ይህ ደግሞ በእግር ኳስ የሚያጋጥም በመሆኑ ተቀብለነዋል፡፡”
” አንድ ጎል አስቆጥረው ያቺን ውጤት ለማስጠበቅ በሙሉ ሀይላቸው ያለመጫወት ችግር ይታያል፡፡ እንግዲህ ይህ ደግሞ ጫናው ያመጣው ነው፡፡ ከዚህ ጫና ለመውጣት እንሰራለን፡፡”
” ጥሩ ኳስ እየተጫወተ ያለ ቡድን ነው፡፡ ከመጀመርያውም ከኋላ መስመር ክፍተቶች አሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የሚታወቅ ነው እነዚህን ድክመቶች ለማረም ጥረት እናደርጋለን፡፡”