የጨዋታ ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ደደቢት በኤፍሬም አሻሞ ግብ ታግዞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ታህሳስ 14 ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ላይ ዳዊት ፍቃዱ በ5ኛው ደቂቃ በግንባሩ ሞክሮ ከወጣበት ኳስ ውጪ የሚጠቀስ ሙከራ ያልታየ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች የተመጠነ ኳስ ለአጥቂዎች ለማድረስ ተቸግረው ታይተዋል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ቀስ በቀስ ወደጨዋታው ስልት የገቡ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ደደቢቶች በበኩላቸው በረጅም ለአጥቂዎች የሚጣሉ ኳሶችን ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ዳዊት ማሞ እና አማረ በቀለ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ደደቢት በሺመክት ጉግሳ እና ዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት የተፈጠሩ የግብ ዕድሎችን መጠቀም አልቻለም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች እና የአጨዋወት ስልት ለውጥ ያደረጉት ደደቢቶች ወደግብ በመድረሱ  በኩል የተሻሉ ነበሩ፡፡ የፕሪምየር ሊጉን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ የሚመራው ጌታነህ ከበደ በ48ኛው ደቂቃ ከአስራት መገርሳ የተሰጠውን ኳስ ተቆጣጥሮ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም መጠቀም ያልቻለበት ፤ እንዲሁም በ54ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከ25 ሜትር ርቀት የመታው ቅጣት ምት የግቡን ቋሚ መትቶ የወጣበት አጋጣሚዎች የሁለተኛው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ሳምሶን ጥላሁንን ተክቶ ወደሜዳ የገባው ኤፍሬም አሻሞ በ85ኛው ደቂቃ ከጌታነህ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥኑ ውስጥ ይዞ በመግባት ደደቢትን አሸናፊ ያደረገች ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ አስቆጥረው አቻ ለመሆን ጥረት ያደረጉ ቢሆንም አማረ በቀለ እና ዘሪሁን ብርሃኑ ከርቀት የመቷቸው ኳሶች ዒላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም፡፡

ደደቢት ድሉን ተከትሎ በመሪነት ፉክክሩን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በ14 ነጥብ በቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ክፍያ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በ5 ነጥብ እና 3 የግብ ዕዳ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘውን ኤሌክትሪክ ብቻ በመብለጥ በ15ተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡

 

የአሠልጣኞች አስተያየት

 

ስዩም ከበደ – አዲስ አበባ ከተማ

“የእኛ ልጆች የሚችሉትን አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡”

“በአጥቂ ስፍራ ከፍተኛ ችግር አለብን፡፡ ትክክለኛ የፊት አጥቂም አለን ማለት አልችልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመሃል ተከላካይ ቦታ ላይ የሚሰለፉት ሁለቱ ተጫዋቾቻችን ተጎድተውብናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቡድኑን እየጠጋገንን እየተጫወትን ነው ያለነው፡፡”

“ዛሬ ቢያንስ ነጥብ ተጋርተን መውጣት የምንችልበት አጋጣሚው ነበረን፡፡ ያገኘነውን አጋጣሚ መጠቀም አለመቻላችን እንደ ክፍተት የምናየው ነው፡፡ እግርኳስ በስህተት የታጀበ ነው፤ እንግዲህ ክፍተቶቻችን ይህን ውጤት እንድናጣ አድርጎናል፡፡”

“ለሁለተኛው ዙር የአጥቂ ክፍላችንን ለማጠናከር እየሰራን እና ከሀገር ውስጥም ከውጪም ተጫዋቾችን እያየን ነው ያለነው፡፡”

አስራት ሃይሌ – ደደቢት

“ይህ ጨዋታ አዲስ አበባ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ አካባቢ እንደመገኘቱ እና ጨዋታውም ለነሱ ወሳኝ እንደመሆኑ በጣም የፈራሁት ጨዋታ ነበር፡፡ ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆኑብን እርግጠኛ ነበርኩ፤ ያሰብኩትም ሆኗል፡፡ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል፤ እነዚህን አጋጣሚዎች ግን አልተጠቀምንባቸውም፡፡”

“ከእረፍት በኋላ አጨዋወታችንን ለወጥ አድርገን ገብተናል፡፡ ዳዊት ተደራቢ አጥቂ ሆኖ እንዲጫወት እና የኤፍሬምን ፍጥነት ለመጠቀምም በሚል ቅያሬዎችን አድርገናል፡፡ በመጨረሻ የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል፤ በእግርኳስ ማሸነፍ ነው ትልቁ ነገር፡፡ ማን ጥሩ ተጫወተ የሚለው ነገር እኔን አያሳስበኝም፡፡ ቡድኔ የሚፈልገውን 3 ነጥብ አግኝቷል ማለት እችላለሁ፡፡ ዛሬ ቡድኑ የማሸነፍ መንፈስ ይዞ እንዲሄድ ነው ፍላጎቴ የነበረው፡፡”

“ደደቢት ስኳዱ  በጣም ጠባብ ነው፡፡ ምንም ልምድ ያለው ተቀያሪ ተጫዋች የለንም፡፡ አሁንም የምናገረው ቡድኑ እኔ ወደምፈልገው የጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ አልገባልኝም፡፡ በሂደት ግን ይህ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ጊዜ ስላለን ምናልባትም እስከ ሁለተኛው ዙር የበለጠ ጥሩ ቡድን እናያለን ብዬ አስባለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *