በ8ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ሶዶ ላይ ወልድያን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፎ ከ4 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ተመልሷል፡፡
ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ተመልካች በተከታተለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በመከላከል ረገድ ጠንካራ ብቃት የታየ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች ጨዋታው ከተጀመረ አንስቶ ከፍተኛ የሆነ ብልጫ ወስደው ተጭነው ተጫውተዋል፡፡ በአላዛር ፋሲካ ፣; በዳግም ንጉሴ እና በበዛብህ መለዮ አማካኝነት ያደረጓቸው ጠንካራ የጎል ሙከራዎችም ለዚህ እንደ ማሳያ የሚቀርብ ነው፡፡ አድርገዋል
በ28ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ብርሃኑ የመታውን የማዕዘን ምት ግልፅ በሆነ ሁኔታ አንዱአለም ንጉሴ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት መሳይ አንጪሶ ወደ ጎልነት በመቀየር ባለሜዳዎቹ 3 ነጥብ ያገኙበትን ግብ አስመዝግቧል፡፡
ወልዲያ አልፎ አልፎ ወደ ፊት ለመሄድ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ የተሳካ የጎል ሙከራ ሳያደርግ የመጀመርያው አጋማሽ በወላይታ ድቻ 1-0 መሪነት እረፍት ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁሉም ረገድ ብልጫ ወስዶ ሲጫወት በተለይ በደጋፊው አድናቆት እየተቸረው ያለው እና ተቀይሮ በመግባት በሚያገኘው አጋጣሚ አቅሙን እያሳየ የሚገኘው ዳግም በቀለ እጅግ ለጎል የቀረቡ ያገኛቸውን የጎል አጋጣሚዎች ግብ ጠባቂው ኤሚክሪል ቤሊንጌ ባያድናቸው የጎል ልዩነቱ ከዚህም የሰፋ የሚሆንበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ድቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ ከዳግም በተጨማሪ በአላዛር ፋሲካ አማካኝነት በተደጋጋሚ የጎል እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ኳሱ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው መሳይ አንጪሶ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አሰተያየት
መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ
ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ነጥብ ከመጣላችን ጋር ተያይዞ በተወሰነ መልኩ ጫና ውስጥ ነበርን፡፡ በመሆኑም በዛሬው ጨዋታ ምንም እንኳ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል በጠባብ ውጤት ብናሸንፍም ከዚህ በላይ ጎል አስቆጥረን ማሸነፍ ነበረብን፡፡ ዋናው ለኛ አስፈላጊ የነበረው ሶስት ነጥብ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ ”
ንጉሴ ደስታ – ወልድያ
“ጨዋታውን እንዳያችሁት ራሳችን በሰራነው ስህተት ዋጋ ከፍለን ወጥተናል፡፡ ከእንደነዚህ ያሉ ስህተቶች መማር እንደሚገባን አስገዝቦናል፡፡ በተረፈ የመከላከል እና ኳስ የመቆጣጠር አጨዋወታችን ጥሩ ነው”
” ጎል የማስቆጠር አቅማችን በጣም አናሳ ነው፡፡ እዚህ ላይ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ችግር የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የዝግጅት እጥረት ፣ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በሚፈለገው መልኩ አለማድረጋችን ጎድቶናል፡፡ በአጠቃለይ በቀጣይ ጨዋታዎች እዚህ ላይ በሚገባ ሰርተን እንመጣለን”