በኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረገው ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያ አዲስ አበባ ከተማን 2-1 በመርታት ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመስግቧል፡፡
ጨዋታው 29ኛው ሰከንድ ላይ የአዲስ አበባ ከተማው የፊት አጥቂ ኃይሌ እሸቱ ከመሀል የተላከለትን ኳስ በመከላከያዎች የተከላካይ መስመር መሀል ይዞ በመግባት የውድድር አመቱን ፈጣን ጎል አስቆጥሯል።
በሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ሚገኙት አዲስ አበባዎች በጨዋታው መጀመሪያ ያገኟትን ይህች ጎል መነሳሻ ሆናቸው ተጨማሪ ጎሎችን ያስቆጥራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካላቸው ቀርቷል ። ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ከተጋጣሚው የተሻለ የነበረ ሲሆን በአቤል ዘውዴ እና ዘሪሁን ብርሀኑ አማካይነት የግብ ሙከራዎችን አድርጎ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።
በጨዋታው በፍጥነት ጎል ያስትናገዱት መከላከያዎች በበኩላቸው ከተጋጣሚያቸው በእጅጉ የላቀ እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችሉም ቀስ በቀስ ወደጨዋታው መመለሳቸው አልቀረም። በዚህም በ10ኛው ደቂቃ በማራኪ ወርቁ ካደረጉት ሙከራ በኋላ በባለፈው ሳምንት ጨዋታ ላይ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ባለድል ባደረገው ሳሙኤል ታዬ አማካይነት በ40ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎል አግኝተዋል። አማካዩ ከማራኪ ወርቁ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ነበር ጎሏን ያስቆጠረው።
በጣም የተዳከመ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት እና ተመልካቹ በብርድ ተቆራምቶ ቁጥሩም ጨዋታው በገፋ ቁጥር እየተመናመነ በሄደበት በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባዎች የተጫዋች እና የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ግቦችን ለማግኘት ኳስን ተቆጣጥረው በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ክፍተቶችን ለማግኘት ሞክረዋል። የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ማግኘት ያልቻሉት መከላከያዎችም ለሁለት የፊት አጥቂዎቻቸው ረጅም ኳሶችን በመላክ እና ከመስመር ሚነሱ ኳሶችን ለመጠቀም በመሞከር ተጫውተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ ላይ በያዝነው ወር ድንቅ እንቅስቃሴ እያሳየ አሚገኘው ግዙፉ የግራ መስመር ተሰላፊ ቴዎድሮስ በቀለ በግል ጥረቱ ተጠቅሞ በግራ በኩል ወደ አዲስ አበባዎች የግብ ክልል ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ ወደውስጥ ሲያሻማ ምንይሉ ወንድሙ አግኝቶ በቀላሉ የጦሩን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።
ከዚህ ጎል ውጪ መከላካዮች በ74ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ በቀለ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የላከለትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከናትን እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም ቴዎድሮስ በቀለ የአዲስ አበባ ተከላካዮችን በሚያስገርም መልኩ አልፎ የሞከረው እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ የቡድኑ ጥሩ ሙከራዎች ነበሩ። በተለይም የ81ኛው ደቂቃ ሙከራ በእለቱ ብርድ ተሳስሮ የነበረውን ተመልካች ለአፍታ ሞቅ ያረገ ሆኖ አልፏል።
በ59ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ዘውዱ ሞክሮት ወደውጪ ከወጣበት ሙከራ ሌላ የነበራቸውን የመሀል ሜዳ የበላይነት ያለቀላቸውን የጎል እድሎች ለመፍጠር ያልተጠቀሙበት አዲስ አዳጊዎቹ አዲስ አበባዎች የአቻነት ጎል ሳያቆጥሩ አምስተኛ ተከታታይ ሽንፈት ለመቅመስ ተገደዋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ሻለቃ በለጠ ገ/ኪዳን – መከላከያ
” የዛሬውን ጨዋታ በድል ተወጥተናል። ግብ ተቆጥሮብንም እያሸነፍን ነው ። የልጆቻችን ብቃት እና ፍላጎት በጣም ጥሩ ነው። በቀጣይም ጥሩ ውጤት እናመጣለን። እንዳያችሁት በርከት ያሉ ጎሎች ማስቆጠር እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን ትልቁ ነገር ከኃላ ተነስተን ማሸነፋችን ነው ። በተጨዋቾቻችን ብቃት እጅግ ደስ ተሰኝቻለው”
” ቴዎድሮስ በቀለ ከተከላካይ ቦታ እየተነሳ ሁለት ጎል አስቆጥሮልናል፡፡ ዛሬም ለጥቂት ከመስመር ላይ ነው የወጣበት። እንዳገባ ነው ምቆጥረው ። ዋናው ማግባቱ ብቻ አይደለም እያሳየ ባለው ብቃት እና ፍላጎት ረክቻለው ”
” አጥቂዎቻችን አንቱ የሚባል ስም ባይኖራቸውም ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነው። ምንይሉ ከB ጀምሮ እዚሁ ያደገ ተጨዋች ነው። እንደምታውቁትም ከጉዳት እና ከቀዶ ጥገና ነው የተመለሰው። አጥቂዎቼ በሚያረጉት እንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ባዬ ገዛሀኝም ቀላል ልምምድ ጀምሯል። በጥሩ ጤንንትም ላይ ይገኛል በቅርቡ ወደጨዋታ ይመለሳል ብለን እንጠብቃለን።”
ስዩም ከበደ – አዲስ አበባ ከተማ
” በዛሬው ጨዋታ ያው እኛ ነጥባችን ዝቅተኛ ነው። በደረጃው ግርጌ ነው ምንገኘው፡፡ ከዛ ለመነሳት ጥረት ለማድረግ ነበር የገባነው ። በአጠቃላይ ተጨዋቾቼ የሚችሉትን ጥረት አድርገዋል። ጎሎች በስህተት ይቆጠራሉ ። እነዛ አጋጣሚዎች ዋጋ አስከፍለውናል። ”
” የአጥቂ ችግር እንዳለብን ገና ከጅምሩ ደጋግሜ ተናግሪያለው። ባሉን ልጆች ነው ለመንቀሳቀስ የምንሞክረው። ጥራት ያላቸው አጥቂዎች ማግኘት ባንችልም ውጤታችንን በዚሁ ለማቆየት በተለይም የመጀመሪያውን ዙር በዚህ ብንገፋው በሁለተኛው ዙር አማራጮችን ከጋና ፣ ከካሜሩን እና ከኬንያ እየሞከርን ነው። ባጠቃላይ ግን ልጆቹ የሚችሉትን አድርገዋል። ”
” እየመራን መሸነፋችን ከማሸነፍ እየራቅን በመምጣታችን የማሸነፍ ስነልቦናችን ከመዳከሙ ጋር ይያያዛል። ዛሬም ትናንሽ ክፍተቶች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን። ማሸነፍ ባንችል አቻ መውጣት ነበረብን። ከዚህ በኃላ ማድረግ የምንችለው እስከመጨረሻው ድረስ መታገል ፣ በጎደሉን ቦታዎች የምንገኘውን ነገር ማስተካከል እና የልጆቻችንን ስነልቦና ሊያድግ ሚችልበትን መንገድ ማስተማር እና ማንቃት ነው። “