በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ መርሃግብር ታላቁ የሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና በኢኮ ፌቨር ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹን በመርታት የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል፡፡
ለወትሮውም ቢሆን በከፍተኛ የደጋፊዎች ታጅቦ የሚካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬም እንደወትሮው ከጠዋት 12፡30 ጀምሮ የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ካንቦሎጆ አካባቢ መሳባሰብ ጀምረው ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑም ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመተበባር ከወትሮው በተለየ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለጨዋታው በሰላም መጠናቀቅ እክል እንደነበሩ በስፋት ሲነገርላቸው የነበሩትን መጠጥ ቤቶች ጨምሮ በስታዲየሙ ዙሪያ የሚገኙ ሱቆቹን ሙሉ ለሙሉ በመዝጋት ልዮ ጥበቃ ሲያስደርግ አርፍዷል፡፡
ሌላው በዛሬው እለት የታየውና ይበል የሚያሰኘው ሌላኛው ነጥብ ለወትሮው ይታይ የነበረውን ረጃጅም የደጋፊዎችን ሰልፍ ለማስቀረት ታሳቢ የተደረገ በሚመስል መልኩ የስታዲየሙ በሮች ከ6፡00 ጀምሮ ተከፍተው ደጋፊዎች እንዲገቡ መደረጉ ነበር፡፡
10፡00 ሲል በተሟሟቀ የደጋፊዎች ድጋፍ ታጅቦ የተጀመው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባለፈው ሳምንት ወላይታ ድቻን 2-0 ካሸነፈው ቡድናቸው በልምምድ ላይ ጉዳት የገጠመውን በሀይሉ አሰፋን ብቻ በራምኬል ሎክ ተክተው በተመሳሳይ 4-3-3 አሰላለፍ፤ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግም ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያየው ቡድን ፊት ላይ ሳሙኤል ሳኑሚን እና ሳዲቅ ሴቾን አስወጥተው ከአራት ጨዋታ በኃላ ቅጣቱን ያጠናቀቀውን አስቻለው ግርማን እና ያቡን ዊልያምን በማስገባት በተመሳሳይ 4-3-3 አሰላለፍ ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡
የመጀመሪያ 15 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሀል ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ኳሶች በስተቀር እምብዛም የረባ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡
የተቀዛቀዘ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሲጥሩ ተስተውሏል በዚህም አጋማሽ በ19ኛው፣21ኛው እና በ23ኛው ደቂቃ ላይ ያቡን ዊልያም ፣ጋቶች ፓኖም እና ኢልያስ ማሞ ከርቀት ምንም እንኳን ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ባይሆኑም የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
በ26ኛው ደቂቃ በግራ መስመር አቅጣጫ ከተገኘችው ቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ ያሻማውን ኳስ ናይጄሪያዊው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ኤኮ ፊቨር አስቆጥሮ ቡናማዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጲያ ቡናዎች በተሻለ ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል በአንፃሩ ከግቧ መቆጠር በኃላ የተናቃቁ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በርከት ያሉ ኳሶችን ከርቀት እንዲሁም ከከቋሙ ኳሶች ሲምክሩ ተስተውሏል፡፡ ከነዚህም ሙከራዎች መሀል በ41ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ታመነ ከቀኝ መስመር አሻምቶ ሳልሀዲን ሰኢድ በግንባር የሞከራትና ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘበት ኳስ ብቻ ኢላማዋን የጠበቀች ነበረች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሩ በፊት በዛሬው እለት የቀብር ስነስርአቱ ለተፈፀመው ለጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር የተጀመረው፡፡
በዚሁ ሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ቡድኖች በንፅፅር ከመጀመሪያው ደከም ያለ እንቅስቃሴን አሳይተዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ሆላንዳዊው ማርት ኖይ በ58ኛው እና በ62ኛው ደቂቃ አከታትለው ባደረጓቸው ቅያሬ ያስር ሙጌርዋ እና ናትናኤል ዘለቀን አስወጥተው ደጉ ደበበ እና አዳነ ግርማን በማስገባት የአጨዋወት ቅርፅቸውን በመቀየር የበለጠ ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል በዚህም ተቀይሮ የገባው ደጉ ከሰልሀዲን ጋር በመጣመር የመሀል ተከላካይነት ስፍራውን ሲመሩ ምንተስኖት አዳነ እና አብዱልከሪም ኒኪማ 2 አማካዮች በመሆን ሲጫወቱ ከነሱ ፊት አቡበከር ሳኒ በግራ እንዲሁም ራምኬል በቀኝ የመስመር አጥቂነት ሲጫወቱ አዳነ እና ሰልሀዲን ሁለቱ የፊት አጥቂ በመሆን በ4-2-4 የሚመስል ቅርፅ የበለጠ ቀጥተኛ በመሆን ከመስመር እና በረጃጅም በሚጣሉ ኳሶች ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡
በዚህም በ61ኛው ደቂቃ አበባው ከቀኝ መስመር ያሻማውን ቅጣት ምት ሰልሀዲን ሰኢድ የቡና ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ ያገኘውን ፍፁም ግልፅ የሆነ የማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ65ኛው ደቂቃ ላይ የፊት አጥቂያቸውን ያቡን ዊልያምን አስወጥተው አማካዮን አክሊሉ ዋለልኝን በማስገባት የአማካይ ቁጥራቸው በማብዛት በ4-5-1 በሚመስል ቅርፅ ፈጣኑን የመስመር ተጫዋች አስቻለው ግርማን በአጥቂነት ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡
ከዚህ በኃላ ነበር ኢትዮጵያ ቡናዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ፍፁም በመከላከል ላይ አተኩረው ተስተውሏል በአንጻሩ ፈረሰኞቹ ጨዋታውን የበለጠ በመቆጣጠር በፈጣን የመስመር አጥቂዎቻቸው ወደ መሀል በሚሻሙ ኳሶች አቻ ለመሆን ቢጥሩም በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂ ጥረት አቻ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
የጨዋታውን መጠናቀቅ የምታበስረው ፌሽካ ከተነፋ በኃላ ከወትሮው በተለየ ሙሉ 90ደቂቃውን ቆመው ቡድናቸውን ሲመሩ የነበሩት ሰርቢያዊው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪች ለወትሮው ከሚታወቁበት ቁጥብነታቸው ባፈነገጠ መልኩ በደስታ ብዛት አጥር ላይ ወጥተው ደስታቸውን በከፍተኛ ሆኔታ ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ኒቦሳ ቪሴቪች – ኢትዮጵያ ቡና
“ከትልቅ ቡድን ጋር እንደመጫወታችን ጨዋታው ሳቢ አልነበረም፡፡በተከታታይ ነጥብ በመጣላችን የተነሳ የዛሬው ጨዋታ ውጥረት የነበረበት ስለነበር ደጋፊዎቻችን እንደሚፈልጉት ሳቢ ጨዋታ ማሳየት አልቻልንም፡፡”
“ጨዋታውን በማሸነፋችን ደጋፊዎቻችን እንደዚህ ተደስተው በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ይህን ጨዋታ በማሸነፋችን ደጋፊዎቻችን ለቀጣዮቹ ቀናት ደስተኛ እንደሚሆኑ አስባለሁ፡፡”
“ለኛ በጣም ወሳኝ የሚባል ሶስት ነጥብ ነው ያገኘነው፤በመጨረሻም ደጋፊዎቻችንን ላመሰግን እወዳለሁ፤ ሁልጊዜም ደጋፊዎቻችን እንደዚህ ሲደሰቱ ነው ማየት የምፈልገው በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ከዚህ የበለጠ እናስደስታችኃለን፡፡”
ማርት ኖይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
” በመጀመሪያ አጋማሽ ተጫዋቾቼ ባሳዮት ነገር ደስተኛ አይደለሁም፤ ከዚህ በፊት በለመድነው የአጨዋወት መጫወት አልቻልንም፡፡”
“አንዳንዴ አሰልጣኝ ብትሆንም በተጨዋቾችህ ትገረማለህ፤ ባሳለፍነው ሳምንት በጣም ጥሩ የነበሩ ተጫዋቾች በዛሬው ጨዋታ ላይ ተዳክመው አስተውያለሁ፡፡”
“በእረፍት ሰአት በመልበሻ ቤት ለተጫዋቾቼ ከዚህ በፊት ጨዋታዎች ላይ ስንጫወት እንደነበረው እንዲጫወቱ አዝዣቸው ነበር፡፡”
“በሁለተኛው አጋማሽ እነሱ ለመከላከል በመግባታቸው እና በተደጋጋሚ ተጫዋቾቻቸው በመውደቅ ሰአት በማባከነቸው እና በተጨማሪም ያገኘናቸውን ሶስት እድሎች ባለመጠቀማችን ተሸንፈናል፡፡
“በውጤቱ በጣም አዝኛለሁ በተለይም ሁሌም ከጎናችን ሁነው ለሚያበረታቱን ደጋፊዎቻችን የሚገባ አልነበረም፡፡”