ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ማሊ በወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾች ላይ አበረታች ስራ ከሚሰሩ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ተጠቃሽናት፡፡
በ2012 እና 2013 የአፍሪካ ዋንጫዎች በተደጋጋሚ የሶስተኛ ደረጃነት ያገኘችው ማሊ በአፍሪካ ዋንጫው እምብዛም እንግዳ አይደለችም፡፡ ማሊ በተክለ ሰውነታቸው የገዘፉ እና የአውሮፓ እግርኳስ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ያየዘ የቡድን ስብስብ አላት፡፡ ቡድኑ ከዓመታት በፊት ሊጠቀሱ የሚችሉ ከዋክብቶቹን ሙሉ በሙሉ በማጣቱ አሁን አሁን በአዲስ ትውልድ ወደ ውድድሮች ብቅ ማለት ጀምራለች፡፡ ንስሮቹ በ2015 ከነበራቸው የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ተስፋ አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 10
ውጤት፡ ሁለተኛ (1972) ሁለት ግዜ ሶስተኛ (2012 እና 2013) ሶስት ግዜ አራተኛ (1994፣ 2002 እና 2004)
አሰልጣኝ፡ አሊያን ግሬስ
ማሊ በምድብ አራት ከጋና፣ ግብፅ እና ዩጋንዳ ጋር ተደልድላለች፡፡ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ግሬስ ለምዕራብ አፍሪካ እግርኳስ አዲስ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም ጋቦን እና ሴኔጋል ማስልጠን የቻሉ ሲሆን ማሊን ሲያሰለጥኑ ይህ ሁለተኛ ግዜያቸው ነው፡፡ ማሊ አሁን ላይ በአዲስ ትውልድ ወደ ውድድር በመቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡ ከ20 ዓመት በታች ቡድኗ በአለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ሁለተኛ የወጣ ሲሆን ዕምቅ ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች በማፍራት ላይ ትገኛለች፡፡ በቡርኪናፋሶ ከቀናት በፊት በአቋም መለኪያ የተሸነፈች ሲሆን እንደ ሰይዱ ኬታ አይነት ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች አለማግኘቷ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚኖረውን ጉዞ ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡
ተስፋ
ማሊ በአብዛኛው ወጣት በሆነ ስብስብ መቅረቧ የማሸነፍ ፍላጎትን ለመያዝ በቀላሉ ያስችላቸዋል፡፡ ለሚጠቀሙት የመስመር አጨዋወትም የተመቹ ተጫዋቾችን መያዟ ይበልጥ ጥንካሬዋ ነው፡፡ አጥቂው ባካሪ ሳኮ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ወደ መስመር እየወጣ ስኬታማ እንቅስቃሴ ማሳየት መቻሉ ሌላው አዎንታዊ ጎን ነው፡፡ ንስሮቹ በየትኛውም ጨዋታ ግብ ማስቆጠር የሚችሉ ሲሆን በግብ ማስቆጠር ሚና ላይ የተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ተጫዋቾች መሳተፋቸው በውድድሩ ላይ ሊዘልቁ እንደሚችሉ ማመላከቻ ነው፡፡ ማሊ በቅርብ አመታት ወዲህ ከጋና ጋር ስትጫወት ያላት የጨዋታ አቀራረብ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ሰፊ የበላይነት መያዟ በስነ-ልቦና ረገድ ለዩጋንዳው ጨዋታ ሊጠቅማት ይችላል፡፡
ስጋት
ቡድኑ ግቦችን ቢያስቆጥርም ግቦችን ማስተናገድም ቅርብ ነው፡፡ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ በኮትዲቯር የተሸነፉበት ጨዋታ ይህንን ችግር በደንብ ያስረዳል፡፡ የሚፈጠሩ የግብ እድሎችን መጨረስ አለመቻልም የግሬስ ሰፊው ጭንቀት ነው፡፡ ከጋቦን ጋር ባማኮ ላይ በተደረገው ጨዋታ አጥቂዎቹ የሚያገኙትን እድል ወደ ሰማይ በመስደድ ማሊን ውጤት አሳጥተዋል፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች በዚህኛው ትውልድ አለመኖሩ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞዋ እስከየት እንደሆነ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከታል፡፡
የሚጠበቅ ተጫዋች
ባካሪ ሳኮ ለንስሮቹ ጥሩ ግልጋሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው፡፡ በዘንድሮ የክለብ እንቅስቃሴው አጥጋቢ ባይሆንም ለሃገሩ ባደረጋቸው ጨዋታዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ወንድማማቾቹ ሳምቦ እና ሙስጠፋ ያታባሬም ሌሎች ለተጋጣሚ ተከላካዮች ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ሙስጠፋ ያታባሬ የአየር ላይ ኳስን የመጠቀም ክህሎቱ ጥሩ መሆኑ ለቡድኑ ጥሩ ግልጋሎት እንዲሰጥ ያደርገዋል፡፡ በተከላካይ መስመሩ በቲፒ ማዜምቤ የተሳካ የእግርኳስ ህይወት በማሳለፍ ላይ የሚገኘው ሳሊፍ ኩሊባሊ ይገኛል፡፡ የአየር ላይ ኳስን በመከላከል ደረጃ የተዋጣለት የተከላካይ መስመር ንስሮቹ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የሞናኮው አዳማ ትራኦሬም እና ግብ ጠባቂው ሱማሊያ ዲያኬቴ እና ያኮባ ሲላ ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ማሊ በምድብ ሶስት ከቤኒን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ነበር የተመደበችው፡፡ ካደረገቻቸው ስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎች በአምስቱ ድል ሲቀናት አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርታለች፡፡ ከምድቡ ለማለፍ እምብዛም ያልተቸገረችው ማሊ የተጋጣሚዎቿ ድክመት በቀላሉ አፍሪካ ዋንጫው እንድትቀላቀል አድርጓታል፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ኦማር ሲሶኮ (ኦርለንስ/ፈረንሳይ)፣ ሱማሊያ ዲያኬቴ (ስታደ ማሊያን ደ ባማኮ/ማሊ)፣ ጂጉ ዲያራ (ስታደ ማሊያን ደ ባማኮ/ማሊ)
ተከላካዮች
ሃማሪ ትራኦሬ (ስታደ ሬሚስ/ ፈረንሳይ)፣ የሱፍ ኮኔ (ሊል/ፈረንሳይ)፣ ሳሊፍ ኩሊባሊ (ቲፒ ማዜምቤ/ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ቻርለስ ትራኦሬ (ትሬይስ/ፈረንሳይ)፣ ሞላ ዋጉ (ዩዲኔዜ/ጣሊያን)፣ ኦሳማኔ ኩሊባሌ (ፓናቲኒያኮስ/ግሪክ)፣ መሃመድ ኮናቴ (ራኤስቢ/ማሊ)
አማካዮች
ላሳና ኩሊባሊ (ባስቲያ/ፈረንሳይ)፣ ያኮባ ሲላ (ሞንፒየሌ/ፈረንሳይ)፣ ሳምቦ ያታባሬ (ቨርደር ብሬመን/ጀርመን)፣ ማማቱ ንዳዬ (አርኤስ አንትወርፕ/ግሪክ)፣ ሳምባ ሶ (ካይሰርስፖር/ቱርክ)፣ የቪስ ቢሶማ(ሊል/ፈረንሳይ)፣ አዳማ ትራኦሬ (ኤኤስ ሞናኮ/ፈረንሳይ)፣ ማማዱ ንዳዬ (ትሮይስ/ፈረንሳይ)
አጥቂዎች
ባካሪ ሳኮ (ክሪስታል ፓላስ/እንግሊዝ)፣ ሙስጠፋ ያታባሬ(ካርደሚር ካራቡክስፖር/ቱርክ)፣ ሙሳ ማሪጋ (ቪክቶሪያ ጉሜሬዝ/ፖርቹጋል)፣ ሙሳ ዶምቢያ (ሮስቶቭ/ሩሲያ)፣ ካሊፋ ኩሊባሊ (ጋንቶይስ/ቤልጂየም)
ማሊ የምድብ የመክፈቻ ጨዋታዋን ማክሰኞ ግብፅን በመግጠም ትጀምራለች፡፡