የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-1 ድሬዳዋ ከተማ

በ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ሰጥተውናል፡፡

” በተጫዋቾቼ ከፍተኛ ተጋድሎ ውጤቱን ይዘን ልንወጣ ችለናል” ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

“የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሀዋሳዎች ተጭነው ተጫውተዋል። ተጭነው ሊጫወቱ የቻሉበት ምክንያት የራሳችን የሆነ ታክቲክ ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃት የነሱ ፉል ባኮች በሚያጠቁበት ቦታ ነበር እኛ ስንጠቀም የነበረው፡፡ ብዙ ኳስ እኛ ሜዳ ላይ ይዘዋል። ሶስተኛው አጋማሽ ላይ ሲደርሱ ግን ብዙም ሙከራ አላደረጉብንም፡፡ ያ ደግሞ እኛ የፈጠርነው መንገድ ነው፡፡ 

” ከእረፍት በኋላ ግን እንደ እንቅስቃሴ ጎል ላይ እንደመድረሳችን በጣም የተሻልን ሆነን ቀርበናል፡፡ ያም ሆነ ይህ በአጠቃላይ በፍሰት እና በእንቅስቃሴ ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ፡፡ ግን እኛ ውጤቱን ስለፈለግነው እና ከሜዳችን ውጪ አሸነፈን ስለማናውቅ ታክቲካችንን ተጠቅመን በተጫዋቾቼ ከፍተኛ ተጋድሎ ውጤቱን ይዘን ልንወጣ ችለናል፡፡ ሀዋሳ ስለተሸነፈ ጥሩ ቡድን አይደለም ማለት አይደለም። በእንቅስቃሴም ጥሩ ናቸው፤ ዛሬ ባይሳካላቸውም ነገ የተሻሉ ይሆናሉ፡፡ ”

” የገባብን ጎል ብዙ ነገር አበላሸብን ” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለዛሬው ሽንፈት እና ጨዋታው

” አዲስ አበባ ላይ ስድተኛው ደቂቃ ላይ (ከቡና) ገብቶብን ነበር፤  ዛሬም ገና ሶስተኛ ደቂቃ ገባብን። ምላሽ መስጠት ግን አልቻልንም፡፡ ፍላጎታችን ሊጉን መምራት ወይም ሁለተኛ የመሆን ነበር፡፡ ያ ግን አልሆነም።

” ብትንትን ያለ ነገር ነበር የነበረው። ዛሬ ለመፍጠር ያሰብነው ጎል ማግባት የምችልበትን አጋጣሚ ለማግኘት ነበር።  ዳንኤል እና ደስታ ባልነበሩበት ሰዓት በዳይመንድ ነበር ስንጫወት የነበረው፡፡ አሁን ግን ከመስመር በሚነሳ አጋጣሚን ነበር ለመፍጠር የሞከርነው፡፡ ሁሉንም የፈጠረው ግን መጀመሪያ የገባብን ጎል ብዙ ነገር አበላሸብን። ምክንያቱም የጠበቅነው ነገር አይደለም፡፡

” የመስመር አጨዋወታችን ከዚህ በፊት ጥሩ ስለነበር ያን ለማድረግ አስበን ነበር። ጉጉቱ ከፍተኛ ነው ሜዳ ውስጥ። ተጫዋች ሲገባ ውጪ ያወራነውን ካልተገበረ በጣም ያስቸግራል። ከመስመር ዳኒም ደስታም ያሻማሉ የሚጠቀም ግን የለም፡፡ ”

የግብ እድል በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር

” ኳስ ጨዋታ ላይ የማጥቃት እና የመከላከል ቦታዎች እጅጉን ጉልተው የሚታዩ ቦታዎች ናቸው፡፡ ሶስተኛ ደቂቃ ላይ ጎል ገባብን፤ ይህን የኛ የመከላከል ችግር ነው እንዲፈጠር ያደረገው። ጎሎችን እናገኛለን እንስታለን፤ ይሄ የሚፈጠር ነገር ነው። ብዙ ጊዜ ጭንቅላትህ ውስጥ ውጥረት ካለ እነዚህን ስራዎች መስራት አትችልም፡፡ ተጫዋች ብዙ ጊዜ ሊሳሳት ይችላል። ሲያቀብልም ሊሳሳት ይችላል። ይሄ ደግሞ ጎልቶ አይታይም። ጎልቶ የሚታየው የመከላከል እና አጥቂ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ላይ ነው፡፡ ብዙ እንደርሳለን። ሆኖም እንደምንደርሰው ጎሎችን አናገባም። እንግዲህ ተጫዋቹ መሳሳቱ ሲገባው የሚስተካከል ነው፡፡ ትልቁ ነገር ግን ወደ ጎል መድረስን እየፈፀምን ነው፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *