ዐፄዎቹ ጊዜያዊ አሠልጣኛቸውን በቋሚነት ሾመዋል

አሠልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ በዋና አሠልጣኝነት ሚና ከፋሲል ከነማ ጋር በቀጣዩ ዓመት ለመቆየት ውላቸውን አድሰዋል።

በተጠናቀቀው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ ከቀድሞ አሠልጣኙ ሥዩም ከበደ ጋር ተለያይቶ ዓመቱን በምክትል አሠልጣኙ ኃይሉ ነጋሽ እየተመራ ማገባደዱ ይታወቃል። በቀጣዩ ዓመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሀገራችንን የሚወክለው ቡድኑም ዝግጅቱን ባህር ዳር ከተማ ላይ መቀመጫውን በማድረግ እየሰራ ይገኛል።

ክለቡን በጊዜያዊነት እያሰለጠኑ የነበሩት አሠልጣኝ ኃይሉ ነጋሽም ከደቂቃዎች በፊት በዋና አሠልጣኝነት መንበር የአንድ ዓመት ውል መፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች የነበሩት አሠልጣኝ ኃይሉ ከ2010 ጀምሮ ክለቡን በምክትል አሠልጣኝነት ሲያገለግሉ እንደነበር አይዘነጋም። ከላይ እንደገለፅነውም ዘንድሮ ከአሠልጣኝ ሥዩም ስንብት በኋላ ክለቡን በጊዜያዊነት መርተው 2ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ረድተው ነበር። አሁን ደግሞ ለከርሞ በዋና አሠልጣኝነት ለመዝለቅ የአንድ ዓመት ፊርማቸውን አኑረዋል።

በምክትል አሠልጣኝነት ሚና ሙሉቀን አቡሀይ እንደሚቀጥሉ ሲገለፅ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ የአሠልጣኝ ዘማርያም ምክትል የነበሩት እና ዋናው አሠልጣኝ ከቦታቸው ሲነሱ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በመንበሩ የቆዩት አሠልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ ደግሞ የአካል ብቃት አሠልጣኝ ሆነው የአሠልጣኝ ቡድኑን ተቀላቅለዋል።