ሩዋንዳ ለወሳኞቹ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ዝግጅቷል ዛሬ ጀምራለች

የፊታችን ዓርብ እና ነሐሴ 29 ከዋልያዎቹ ጋር የቻን የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠብቀው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ዛሬ ጅምሯል።

በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ በሚያሳትፈው እና በቀጣዩ ዓመት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ በየዞኑ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሴካፋ ዞን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የደቡብ ሱዳን አቻውን ገጥሞ በሰፋ ውጤት አሸንፎ በመጨረሻው ዙር ከሩዋንዳ ጋር ለመፋለው ዝግጅቱን አዳማ ላይ በመከተም እያከናወነ ይገኛል። ባሳለፍነው ዓርብ እና ዕሁድም ከዩጋንዳ ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ አንዱን ረቶ በአንዱ አቻ ተለያይቷል።

ተጋጣሚያችን ሩዋንዳ በበኩሏ የሊግ ውድድሯን እየጀመረች በመሆኑ ነሐሴ 20 እና 29 ለሚደረጉት ፍልሚያዎች የምታደርገውን ዝግጅት ዘግይታ ለመጀመር ተገዳለች። ከቀናት በፊትም በስፔናዊው አሠልጣኝ ካርሎስ አሎስ ፌረር የሚመራው ቡድኑ ለደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረቡን ዘግበን የነበረ ሲሆን ቡድኑም በትናንትናው ዕለት በሴንት ፋሚሊ ሆቴል ተሰባስቦ በዛሬው ዕለት ልምምዱን ጀምሯል።


ቡድኑም ረፋድ ላይ የጂምናዚየም ስራዎችን ከሰራ በኋላ የሜዳ ላይ ልምምድ እንዲሁም ቀትር ላይ የክፍል ውስጥ የታክቲካል ቪዲዮ ትምህርት እንደወሰደ ተመላክቷል። ብሔራዊ ቡድኑ ነገም በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ልምምዱን ሰርቶ ረቡዕ የመጀመሪያ ጨዋታው ወደሚደረግበት ታንዛኒያ ዳሬ ሰላም እንደሚያመራ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የመጀመሪያ ጨዋታ ዓርብ በታንዛኒያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከ9 ቀናት በኋላ ሩዋንዳ ላይ በሁዬ ስታዲየም ይከናወናል።