የሲዳማ ቡና ምክትል አሰልጣኝ ታውቀዋል

አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ረዳት አሰልጣኛቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቀመጫውን በታደሰ እንጆሪ ሆቴል በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን በዋና አሰልጣኝነት ከሾመ በኋላ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እንዲሁም ውላቸው ተጠናቆ የነበሩ የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት በማደስ ወደ ዝግጅት መግባቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ የቀድሞው ረዳት አሰልጣኙ ቾንቤ ገብረህይወትን ከዓመታት ቆይታ በኋላ በድጋሚ በረዳት አሰልጣኝነት ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡

ሥልጠናን በሀዋሳ ከተማ የወጣት ቡድን ውስጥ መጀመር የቻሉት አሰልጣኙ በመቀጠል ወደ ሲዳማ ቡና በማምራትም ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት እና ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በዋና አሰልጣኝነት ከዚህ መስራት ችለዋል፡፡ በደቡብ ፖሊስ ፣ ነቀምት ከተማ እና የተጠናቀውን የውድድር ዘመን በሀላባ ከተማ የዋና አሰልጣኝነት ሚናን ሲሰጡ የቆዩት አሰልጣኙ የአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን ጥሪ ተከትሎ በይፋ የሲዳማ ቡና ረዳት አሰልጣኝ በመሆን በድጋሚ ወደ ክለቡ መቀላቀል ችለዋል፡፡