ቡናማዎቹ በዲቫይን ዋቹኩዋ ብቸኛ ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን 1ለ0 መርታት ችለዋል።
12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫውን ሲወስዱ 6ኛው ደቂቃ ላይም ዲቫይን ዋቹኩዋ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት በመታው እና ግብ ጠባቂው ስንታየሁ ታምራት በመለሰው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል።
በርካታ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረሱ በኩል ብልጫውን ያስቀጠሉት ቡናማዎቹ 26ኛ ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ይታገሱ ታሪኩ ከረጅም ርቀት በድንቅ ሁኔታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ስንታየሁ ታምራት በግሩም ብቃት አስወጥቶበታል።
ሀዲያዎች ተደራጅተው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ሲቸገሩ ቶሎ ቶሎ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉት ቡናማዎቹ 45ኛ ደቂቃ ላይ በዲቫይን ዋቹኩዋ አማካኝነት ከቅጣት ምት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ጎሎቹን አስቆጥሮ ለማሸነፍ ልዩ ትኩረት በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እና ሳቢ የሆነ ጨዋታን አስመልክተውናል። ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል በመመስረት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የሚችሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ከመረብ ጋር ለማዋሃድ የሀዲያ ተከላካዮች ከባድ ፈተና ሆነውባቸው ነበር። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በረጃጅም ኳሶቻቸው ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
ነገር ግን 60ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታው ላይ መሪ የሆኑበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። አንተነህ ተፈራ ከመሃል ሜዳ ያቀበለውን ኳስ ዲቫይን ዋቹኩዋ በድንቅ ፍጥነት ኳሱን በመንዳት ሳጥን ውስጥ ደርሶ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በብዙ ተጫዋቾች ወደ ኋላ በመመለስ መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎችን አልፎ ግብ ማስቆጠር ከባድ ሆኖባቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ደረጃቸውንም ባህር ዳር ከተማ እስኪጫወት በጊዜያዊነት ወደ 2 ከፍ ማድረግ ችለዋል።