ሪፖርት | የአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ጎል ፈረሰኞቹን ባለ ድል አድርጓል

ሪፖርት | የአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ጎል ፈረሰኞቹን ባለ ድል አድርጓል

በ28ኛ ሳምንት የረፋድ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌትሪክን 1-0 በመርታት ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሽንፈት መልስ ያሬድ የማነህ እና ጌታሁን ባፋን በማሳረፍ አብዱላዚዝ አማን እና ቢንያም በቀለ ተክተው ጨዋታውን ሲጀምሩ በአንፃሩ ከድል የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው አፈወርቅ ኃይሉ፣ ፀጋ ከድር እና ቢንያም ፍቅሩ አስወጥተው ዳግማዊ ዓርዓያ፣ ሀብታሙ ጉልላት እና ፍፁም ጥላሁንን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፌደራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ እየተመራ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ቀጥተኛ ኳሶች ወደ ሁለቱ ሳጥኖች በማድረስ አደጋ ለመፍጠር በታሰበው እንቅስቃሴ ግብ ለማስተናገድ እምብዛም አልቆየም። 10ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተከላካይ ቢንያም በቀለ ከሜዳቸው ለመውጣት የተቀበለው ኳስ በተከቢው ሁኔታ ኳሱን ባለመቆጣጠሩ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ፍፁም ጥላሁን ያገኘውን ኳስ ግብ ጠባቂው ኢዲሪሱ ያቋረጠውን አማኑኤል ኤርቦ ደርሶ ጎል አድርጎታል።

ከጎሉ በኋላ ፈረሰኞቹ ጠንቀቅ በማለት የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን መጠባበቅን ምርጫው  ሲያደርጉ በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ ኮሶችን ወደ ፊት በማድረስ አደጋ ለመፍጠር በተደጋጋሚ ቢንቀሳቀሱም ግብ ፊት ሲደርሱ መረጋጋት ባለመቻላቸው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል። የአጋማሹ መጠናቀቂያ አስር ደቂቃም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ከኃይል አጨዋወት ጋር እያስመለከተን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት ሲመለሱ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ፈጣን የማግባት ዕድል ቢያገኙም አቤል ሐብታሙ መጠቀም ሲገባው ለናትናኤል ገብረጊዮርጊስ መስጠትን መርጦ የናትናኤል ሙከራ ውጤታማ ሳይሆን ወደ ውጭ ወጥቷል። ፈረሰኞቹ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እየተወሰደባቸው ያለውን ብልጫ እንዳይቀጥል ለማድረግ ሻይዱ ሙስጠፋ እና አብርሃም ጌታቸውን ቀይረው ቢያስገቡም የሚሰነዝርባቸው ጥቃት ቀጥሎ 58ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አብዱላዚዝ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን አቤል ሀብታሙ በግንባሩ በመግጨት የተሻለውን ሙከራ አድርገዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የጨዋታው እንቅስቃሴ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ እንዲያመዝን ማድረግ ቢችሉም የመጨረሻ ኳሶቻቸው በስህተት የተሞሉ መሆናቸው እና ጠንካራውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል አጥር ጠሰው ለመግባት መቸገራቸው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ጨዋታው እያከበደባቸው መጥቷል።

ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እጅግ ለጎል የቀረቡ ሁለት ሙከራዎችን አድርገዋል። 87ኛው ደቂቃ ላይ አብዱላዚዝ አማን ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ የመታውን ጠንካራ ምት ግብ ጠባቂው ባህሩ የመለሰበት እንደገና 90ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ገብረማርያም ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ግብ ጠባቂው ባህሩ በጥሩ ቅልጥፍና ጎል እንዳይሆን ከልክሏቸዋል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ መከላከል 1-0 አሸናፊነት እንዲቋጭ ሆኗል።