ስሑል ሽረ እና ፋሲል ከነማን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሦስተኛ መርሐ-ግብር ነው።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ የአቻ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት ስሑል ሽረዎች ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።
በቅርብ ሳምንታት በስሑል ሽረ የሚታየው ድክመት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜ ነው። ቡድኑ ምንም እንኳን ከተከታታይ ሽንፈቶች ማገገም ቢችልም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርቶ ወደ ድል መንገድ መመለስ አልቻለም። ቡድኑ በሊጉ በአስራ አንድ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ቀዳሚ ከሆነው ድሬዳዋ ከተማ በአንድ አንሶ በአስር ጨዋታዎች አቻ መለያየቱም ከነጥብ መጋራት መላቀቅ አለመቻሉ ማሳያ ነው። በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ድል ማስመዝገብ በሚገባቸው ወሳኝ ወቅት ላይ እንደመሆናቸው ከስምንት የጨዋታ
ሳምንታት በኋላ ድል ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቅርብ ሳምንታት ጥሩ ለውጥ ያመጣው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬው በነገው ዕለት መቀጠል የሚገባው የቡድኑ አወንታዊ ጎን ነው።
በሰላሣ አራት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ዐፄዎቹ በብዙ መለኪያዎች የላቀ ብቃት አሳይተው ካሳኳቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ መቀዛቀዞች አሳይተዋል። ከተጠቀሱት መርሐ-ግብሮች በኋላ በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ በተለይም በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ጥንካሬ ማጣቱ ከድል ጋር አራርቆታል። ቡድኑ ተከታታይ ድሎች ባስመዘገበባቸው ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ከማስቆጠሩም በላይ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም ቀጥለው በተካሄዱ የመጨረሻ ሦስት መርሐ-ግብሮች ግን አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ የፊት መስመሩ መዳከም አንድ ማሳያ ነው። ይህንን ተከትሎ የተጠቀሰው የፊት መስመር ድክመት ማረም በነገው ዕለት ከቡድኑ የሚጠበቅ ስራ ሲሆን ተጋጣሚው በቅርብ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ ውስን መሻሻሎች ያሳየ እንደ መሆኑ ግን የሚጠብቃቸው ፈተናው ቀላል ይሆናል ተብሎ አይገመትም።
በስሑል ሽረ በኩል ኬቨን አርጉዲ በጉዳት ነፃነት ገብረመድኅን ደግሞ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሳተፉም። ፋሲል ከነማዎች እዮብ ማቲያስ እና ሀብታሙ ተከስተን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም፤ ኪሩቤል ዳኜ በአንፃሩ ከጉዳት የሚመለስ ቢሆንም መሰለፉ ግን አጠራጣሪ ነው።
የተሰረዘውን የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በታሪካቸው ሦስት ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ ፋሲል ከነማ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማ አራት ግቦች ሲያስቆጥር ስሑል ሽረ አንድ ግብ አስቆጥሯል።