ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ተጋጣሚያቸውን የሚያውቁበት ቀን ይፋ ሆነ

ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ተጋጣሚያቸውን የሚያውቁበት ቀን ይፋ ሆነ

የካፍ ክለቦች ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉት ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዙር ተጋጣሚያቸውን የሚለዩበት ቀን ከዚህ ቀደም ማጋራታችን ይታወቃል። አሁን ደግሞ ካፍ ቀኑን አረጋግጦ ይፋ አድርጓል።

ቀደም ሲል ከሞሮኮው የዜና ምንጭ ባገኘነው መረጃ ተንተርሰን መረጃውን ለአንባቢያን አጋርተን በነበረው መሠረት የ2026/27 የካፍ ክለቦች ውድድር የመጀመሪያ ዙር የዕጣ ድልድል ሥነ-ሥርዓት ሐሙስ ሐምሌ 30 በግብፅ ካይሮ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 8:00 ላይ ይደረጋል። በዚህም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሚሳተፈው ሲዳማ ቡና እና በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ አህጉራዊ ጉዞውን የሚጀምረው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጋጣሚዎቻቸውን የሚያውቁ ይሆናል።

ካፍ ለተሳታፊ ክለቦች የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ያሻሻለ ሲሆን በመጀመሪያው ቅድመ ማጣሪያ ዙር የሚሰናበቱትን ጨምሮ እያንዳንዱ ተሳታፊ ክለብ የ50,000 ዶላር ይበረከትለታል። ወደ ምድብ ድልድል የሚያልፉ ክለቦች ደግሞ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በቻምፒየንስ ሊጉ ወደ ምድብ የገቡ ክለቦች ዝቅተኛው ሽልማት 700 ሺህ ዶላር አሸናፊው እስከ 4 ሚልየን ዶላር ያገኛል። በኮንፌደሬሽን ካፕ ደግሞ ወደ ምድብ ለሚያልፉት ዝቅተኛው ሽልማት 400 ሺህ ዶላር ሲሆን የውድድሩ ሻምፒዮን ደግሞ 2 ሚልየን ዶላር ይሸለማል።

የዚህ ውድድር የመጀመርያ ዙር ቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የሚጀምሩ ሲሆን የስታዲየም ማረጋገጫ ያላገኙ ክለቦች ጨዋታቸውን በካፍ በተፈቀዱ የሌላ ሀገራት ስታዲየሞች ለማድረግ ይገደዳሉ።