👉”ደጋፊዎቹ እኔን ለማየት ወደ ስታዲየም ከመጡ፣ እኔ ደግሞ…”
👉”ፋይናንስ ለአንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋች የራሱ ቦታ አለው። ዋናው ምርጫዬ ግን…”
👉”ስለ ውበትም ሆነ ስለ እግር ኳስ ችሎታዬ የሚሰጡት አስተያየት…”
👉”ደጋፊዎች ሜዳ ላይ የማይበገር፣ የምትዋጋ እና ለቡድኑ ስኬት ሁሉንም ነገር የምትሰጥ ሴናፍን ያያሉ።”

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ድንቅ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች መካከል ሴናፍ ዋቁማ አንዷ እንደሆነች ብዙዎች ይስማማሉ። ከዚህ ቀደም በጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ፣ አዳማ ከተማ ፣ መቻል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተለያዩ የዕድሜ እርከኖች የተጫወተችው እና በግሏ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆና ያጠናቀቀች እንዲሁም የሊጉን ዋንጫ ያነሳችው አጥቂዋ ከቀናት በፊት ወደ ታንዛኒያው ክለብ ሲምባ ኪዊንስ ያመራችበትን ዝውውር ፈፅማለች። ሶከር ኢትዮጵያም ስለዝውውሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከተጫዋቿ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
አዲስ የእግርኳስ ሕይወት በአዲስ ሀገር ጀምረሻል። እስቲ ከሲንባ ጋር የነበረውን እድል እንዴት እንዳገኘሽና ድርድሩ እንዴት እንደነበረ አጫውቺን?
“ያለፈው የዝውውር ሙከራ ነው ወደ ሲንባ ኩዊንስ የመዛወር እድሉ የተፈጠረው ፤ አሁን ሳይሆን ባለፈው የውድድር ዓመት ነበር። እናም ክለቡ እኔን ለማስፈረም የነበረውን ፍላጎት ባለማቋረጥ በዚህኛው የዝውውር መስኮት በድጋሚ ድርድር ጀምረን ለአንድ ዓመት የሚቆይ ውል በስኬት ተፈራርመናል።”
በክለቡ ልምምድ እንደጀመርሽ አውቃለው። ክለቡን እንዴት አገኘሽው?
“ሲንባ ኩዊንስ በምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ስም እና በርካታ ስኬቶች ያሉት ክለብ ነው። ልምምድ ስጀምር ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር የክለቡን ፕሮፌሽናልነት፣ ለሴቶች እግር ኳስ የሚሰጠውን ትኩረት እና ለአዳዲስ ተጫዋቾች የሚያደርጉትን እንክብካቤ ነው። በቅርቡ ለሚደረገው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ (CECAFA) ራሳችንን እያዘጋጀን ሲሆን ቡድኑ ውስጥ ያለው የፉክክር መንፈስ በጣም ደስ የሚል ነው።”
በሀገር ውስጥም አንቺን ለማስፈረም የሞከሩ ክለቦች አሉ። ሲንባን የመረጥሽው በፋይናንስ ምክንያት ወይስ?
“በሀገር ውስጥ ካሉ ጥሩ ክለቦች ጥያቄዎች እንደነበሩኝ እውነት ነው። ፋይናንስ ለአንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋች የራሱ ቦታ አለው። ዋናው ምርጫዬ ግን ከሀገር ውጪ ወጥቶ አዲስ ፈተናን መጋፈጥ እና ሰፊ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ራስን ማሳየት ስለነበረ ነው። ሲንባ በሊጉም ሆነ በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑ ምርጫዬን ቀላል አድርጎታል።”
የሲንባ ደጋፊዎች ዝውውሩ ይፋ ሲሆን አቀባበላቸው የሚገርም ነበር። አንዳንዶቹ መልክሽን መነሻ በማድረግ ቆንጆ እንደሆንሽና ቀጣይ አመት ስታዲየም እንደማይቀሩ እየተናገሩ ነው። የደጋፊዎችን አቀባበል እንዴት አገኘሽው?
“ዝውውሬ ይፋ ሲሆን በሶሻል ሚዲያ ያደረጉልኝ አቀባበልና የሰጡት አስተያየት በጣም አስገርሞኛል ፤ አስደስቶኛልም። ስለ ውበትም ሆነ ስለ እግር ኳስ ችሎታዬ የሚሰጡት አስተያየት ሜዳ ገብቼ ለክለቡ ጠንክሬ እንድሰራ ተነሳሽነት ይፈጥርልኛል። ደጋፊዎቹ እኔን ለማየት ወደ ስታዲየም ከመጡ፣ እኔ ደግሞ በሜዳ ላይ ግቦችን በማስቆጠር የእነሱን ፍቅር እና እምነት የመመለስ ትልቅ ኃላፊነት አለብኝ።”

የቀድሞ የቡድን አጋርሽ አረጋሽ እዛው ሀገር ነው የምትጫወተው። በዝውውርሽ ሂደት ከአረጋሽ ጋር ያወራሽው ነገር ነበር?
“አላወራንም ነገር ግን አሁን በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ብንሆንም በሀገር ውስጥ የነበረንን ጥሩ ትውውቅ እዚህም እንቀጥላለን፤ ሜዳ ላይ ግን ለየክለባችን እንፋለማለን።”
የአሜሪካ ሙከራሽ በምን ምክንያት መሳካት አልቻለም?
አዎ! ወደ አሜሪካ አቅንቼ ነበር ፤ በእግር ኳስ ውስጥ ብዙ የሙከራ እድሎች ይመጣሉ ፤ አለመሰካቱ እንደ አንድ አማኝ ክርስትያን የእግዚያብሄር ፍቃድ አለመሆኑ ነው የተረዳሁት ፤ እናም የሙከራ ጉዞዎችና ዓለም አቀፍ ልምዶች ብዙ አዳዲስ ነገሮችን፣ ፕሮፌሽናሊዝምንና ጥንካሬን አስተምረዉኛል። አሁን ሙሉ ትኩረቴን እዚህ ታንዛኒያ ላይ አድርጌያለሁ።”
በታንዛኒያ ሊግ ከሴናፍ ምን እንጠብቅ?
“የግብ ማሽንነቴን መቀጠል፣ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና በሴካፋ (CECAFA) ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችያለሁ። ከሲንባ ኩዊንስ ጋር የሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት እና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ረጅም ርቀት መጓዝ ዋናው ግቤ ነው። ደጋፊዎች ሜዳ ላይ የማይበገር፣ የምትዋጋ እና ለቡድኑ ስኬት ሁሉንም ነገር የምትሰጥ ሴናፍን ያያሉ።”
በመጨረሻ ማለት የምትፈልጊው ነገር ካለ?
“እስካሁን ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ መላው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪዎችን እና አዲሶቹን የሲንባ ደጋፊዎችን በጣም ማመስገን እወዳለሁ። ከሀገር ወጥቶ መጫወት የራስን ብቃት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ጭምር መወከል በመሆኑ ኢትዮጵያን በበጎ የሚያስጠራ ስራ ለመስራት ቃል እገባለሁ።”

