ሪፖርት | ስሑል ሽረ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ስሑል ሽረ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በተቆጠሩ ግቦች ስሑል ሽረ እና ፋሲል ከነማ 1-1 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በምሽቱ መርሐግብር ስሑል ሽረን ከፋሲል ከነማ ጋር አገናኝቷል። ስሑል ሽረዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከ ወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ  አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ በተመሳሳይ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ የተጋሩት ፋሲል ከነማዎች ይዘውች ከገቡት አሰላለፍ ተካልኝ ደጀኔን በኪሩቤል ዳኜ በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

12:00 ሲል የተጀመረው ይህ ጨዋታ ከጅማሮው አንስቶ ጎሎችን ያስመለከተን ጨዋታ ነበር። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ግዛው ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በመሆን የተከላካዮቹን መዘናጋት አስተውሎ ሩጦ ለወጣለት ኪዛ ማርቲን ሰንጥቆ የሰጠውን ኳስ ኪዛ ወደ ግብነት በመቀየር አፄዎቹን መሪ አድርጓል።

ነገር ግን የፋሲል ከነማ መሪነት መቆየት የቻለው ለሁለት ያክል ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ረጃጅም የአየር ላይ ኳሶችን ምርጫቸው በማድረግ ግብ ለማግኘት ይሞክሩ የነበሩት ስሑል ሽረዎች አቻ የሆኑበትን ግብ 13ኛው ደቂቃ ላይ ማግኘት ችለዋል። መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገው እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ያሻማውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሲል ከነማዎች ተረጋግተው በኳስ እና በእንቅስቃሴ አንፃር የጨዋታውን ብልጫ በመውሰድ ደጋግመው ለማጥቃት ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ነገርግን ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ኳስን ከመረብ ጋር ማገናኘቱ ላይ ድክመት ተስተውሎባቸዋል። ስሐል ሽረዎች በመከላከሉ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመከላከል የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጃጅም የአየር ላይ ኳሶች ከተከላካይ ጀርባ በመጣል የፋሲሎችን የግብ ክልል መጎብኘት ችለዋል። ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ማርቲን ኪዛ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ በረከት ግዛው ሳጥን ውስጥ በመግባት ቢመታውም ግብጠባቂው አውጥቶበታል። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ሌላ ግብ ሳያስመለክተን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከዕረፍት መልስ ሲቀጥል ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ ረገድ ተቀዛቅዘው ቀርበዋል። ስሑል ሽረዎች ከዕረፍት መልስ ያሉትን 20 ያክል ደቂቃዎች የያዙትን ነጥብ ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታን ምርጫቸው በማድረግ ከተጋጣሚ ሰህተትን በመፈለግ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በተቃራኒው ፋሲል ከተማዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳስን መስርተው ወደ ፊት ለመሄድ ፍላጎት ቢኖራቸውም ሁለቱም ቡድኖች አጨራረስ ላይ የጎላ ክፍተት እንዳለ አስመልክተውናል።

ያለ ሙከራ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን እንድንመለከት ያስገደደን ጨዋታ በአጋማሹ ብቸው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 84ኛው ደቂቃ ላይ የስሑል ሽረው  አብዲ ዋበላ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው እንደምንም ጨርፎ በግቡ አግዳሚ በኩል አስወጥቶታል። የመጨረሻወችን አስር ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር ግቦችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።