ከፍተኛ የሆነ ፉክክርን ባስመለከተን ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና መቻል 2-2 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ ሲዳማ ቡናን ከመቻል ጋር ተገናኝተዋል። ሲዳማ ቡናዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሀዋሳ ጋር ነጥቤ ከተጋሩበት ጨዋታ አሰላለፍ መስፍን ሙዜ ፣ ደስታ ዮሐንስ፣ ደግፌ አለሙ፣ አበባየሁ ሀጂሶ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በማሳረፍ በምትካቸው ቶማስ ኢካራ፣ ጊት ጋትኮች፣ ብርሃኑ በቀለ፣ ሬድዋን ናስር እና መስፍን ታፈሰ ወደ ሜዳ ሲገቡ በመቻል በኩል ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ዮሐንስ መንግሥቱ እና ሽመልስ በቀለን በፊልሞን ገ/ጻዲቅ እና በኃይሉ ግርማ በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
10:00 ሲል የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተን ሲሆን የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ተጭነው ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በብዛት መድረስ የቻሉ ቢሆንም የመጀመሪያውን ጥሩ ሙከራ በመሞከር ረገድ መቻሎች ቀዳሚ ነበሩ። 13ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ክእጅ አስጀምረው አለምብርሃን ይግዛው ያቀበለውን ኳስ በረከት ደስታ በቀኝ መስመር የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሁኖ በግራ እግሩ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።
ከአስረኛው ደቂቃ በኋላ ኳስን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በመመስረት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በፈጣን ሽግግር መድረስ የቻሉት መቻሎች 29ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 29ኛው ደቂቃ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ለማራቅ የሞከሩትን ኃይል የሌለው ኳስ ያገኘው አማኑኤል ዮሐንስ ያቀበለውን ኳስ ፊሊሞን ገ/ፃዲቅ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በመምታት ግብ ማስቆጠር ችሏል። አጋማሹም በዚህ ውጤች ተጠናቅቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ሲዳማ ቡናዎች የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ የተመለሱ ሲሆን ሬድዋን ናስር እና ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በማስወጣት አበባየሁ ሀጂሶ እና በዛብህ መለዮ እነሱን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከዕረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው መቅረብ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን 52ኛው ደቂቃ ላይ ሜዳው ላይ የነበሩትን ደጋፊዎች ድባብ የቀየረ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሀብታሙ ታደሰ ከመሀል ሜዳ ከመቻል ተጫዋቾች የነጠቀውን ኳስ ተጫዋቾችን በማለፍ እየነዳ መጥቶ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ቢመልሰውም ያንኑ የተመለሰ ኳስ ያገኘው መስፍን ታፈሰ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
የግቡ መቆጠር ይበልጥ መነቃቃትን የፈጠረባቸው ሲዳማ ቡናዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ በደስታ ደሙ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበን ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ብዘሞ ሳይቆይ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች የድካማቸውን ፍሬ ያገኙበትን ግብ አስቆጥረዋል። 62ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው በዛብህ መለዮ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን ከመመራት ተነስቶ መሪ እንዲሆን ማድረግ ችሏል። በዚህም ግብ የክለቡ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ለየት ያለ አዝናኝ በሆነ መንገድ ደስታቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ያሉት መቻሎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዳንኤል ዳርጌ ያገኘውን ዕድል ወደ ግብነት ለመቀየር ጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ተረባርበው መልሰውታል። ከሁለተኛው ግብ መቆጠር መነሳሳትን የፈጠረባቸው መቻሎች ጫናዎችን ፈጥረው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 72ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር አለምብርሃን ይግዛው ያሻገረውን ኳስ አቤል ነጋሽ በጉልበቱ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።