አዞዎቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች ለመላቀቅ ሐይቆቹ ደግሞ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ የሚፋለሙበት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ወደ ሊጉ ባደጉበት ዓመት ከብዙዎች ግምት ውጭ አስደናቂ ግስጋሴ በማድረግ ላይ የቆዩት አዞዎቹ የቅርብ ሳምንታት ውጤታቸው በሚፈልጉት መንገድ እየሄደላቸው አይደለም፤ ከድል ጋር ከተራራቁም አምስት ጨዋታዎች አስቆጥረዋል።
ኤሌክትሪክን ሁለት ለባዶ ካሸነፈ በኋላ በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈቶች እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከዚህ ቀደም ሁነኛ መሳርያው የነበረው የቀጥተኛ አጨዋወት ጥንካሬው ማጣቱ ከጨዋታዎች ውጤት ይዞ እንዳይወጣ እያደረገው ይገኛል። ቡድኑ የፊት መስመር ጥንካሬው ማጣቱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩበት በሚያሳይ መልኩ የማጥቃት አቅሙ ተዳክሞ በታየባቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐ-ግብሮች አራት ግቦች ያስተናገደው የኋላ መስመሩም በድጋሚ እርጋታውን ያጣ ይመስላል። የነገው ተጋጣሚያቸው ሀዋሳ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስቆጠረና በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ የሚገኝ እንደመሆኑም የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ከመቼውን ጊዜ በላይ ተሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል።
የቡድኑን የወጥነት ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ስራዎች መስራት የሚጠበቅበት አሰልጣኝ በረከት ደሙ በነገው ዕለት የመከላከል አደረጃጀቱን ከማሻሻል በተጨማሪ በፊት መስመር ላይ የግል ብቃት ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ በቀደሙ ጨዋታዎች የነበረውን የማጥቃት ስትራቴጂዎች መልሶ ማግኘት አስፈላጊው ይሆናል።
በሰሞኑ በጥሩ ንቃት ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት ሀዋሳ ከተማዎች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ባሳኳቸው ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችለዋል።
በሰላሣ አንድ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀይቆቹ በወሳኝ ወቅት የሚታይ መሻሻል አሳይተዋል። ቡድኑ ፈታኝ በነበሩ ያለፉት አምስት ሳምንታት ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥቦች አራቱን ብቻ ጥሎ አስራ አንድ ነጥቦች መሰብሰቡ እንዲሁም በጨዋታዎቹ ያሳየው ብቃት ለምን ከወራጅ ቀጠናው እንደወጣ ገላጭ ናቸው። ከሜዳ ላይ ብቃታቸው በተጨማሪ በከተማቸው እና በደጋፊያቸው ፊት መጫወታቸው በብዙ ረገድ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ሀይቆቹ ከአደጋ ዞኖ ያላቸውን የሁለት ነጥቦች ርቀት ለማስፋት የነገውን ሙሉ ነጥብ በጣሙን ያስፈልጋቸዋል። ነገ ድል ማድረግ ከቻለ ከወራጅ ቀጠናው በአምስት ነጥቦች መራቅ መቻሉ እንዲሁም ተከታዮቹ ድሬዳዋ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ በዚህ የጨዋታ ሳምንት እርሰበርስ መገናኘታቸው ተከትሎም ለጨዋታው ትልቅ ትርጉም እንዲሰጠው ያደርገዋል። ቡድኑ በያዘው ውጤታማ ጉዞ ለመዝለቅም የፊት መስመር ጥንካሬውን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ባለፈው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ያልተሰለፈው ቢንያም በላይ ጨምሮ ሁሉም የቡድን አባላቶች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 19 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ 8 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ 6 ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ 5 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 19ኙ የሀዋሳ፤ 16ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።