ሪፖርት | ሀይቆቹ ከአደጋው ቀጠና የራቁበትን ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | ሀይቆቹ ከአደጋው ቀጠና የራቁበትን ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ሀዋሳ ከተማዎች አርባምንጭ ከተማን በእስራኤል እሸቱ ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።


የድል ረሃብ ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች ከሽንፈት መልስ በተመሳሳይ የሦስት  ለውጦች በማድረግ ቻርልስ ሪባኑ፣ ቡታቃ ሸመና እና አሸናፊ ተገኝን  በአንዱዓለም አስናቀ፣ እንዳልካቸው መስፍን እና ፀጋዬ አበራን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሀዋሳዎች ድል በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ከወጡበት የባለፈው ጨዋታ አስተላለፍ ሦስት ለውጦች አድርገዋል። በዚህም ሲሳይ ጋቾ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ማይክል ኦቱሎ አሳርፈው ፍቃደስላሴ ደሳለኝ፣ ቢንያም በላይ እና ዳዊት ታደሰ ተክተዋል።

ፌደራል ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ ባስጀመሩት ይህ ጨዋታ ቡድኖቹ የቀጥተኝነት ጠባይ ባለው ወደ ግብ ቀጣና በሚላኩ ረጅም ኳሶች እያስመለከቱን በዘለቀው 15ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ተባረክ ሄፋሞ ያገኘውን ኳስ ተከላካዮች ተደርበው ካወጡበት በቀር የሚጠቀስ የጠራ ሙከራ ሳንመለከት በ21ኛው ደቂቃ ሀይቆቹ ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል በድንቅ የቡድን ስራ አስቆጥረዋል።

ከሜዳው መሐል ክፍል ቢንያም በላይ የተነሳውን ኳስ ተባረክ ተቀብሎ በጥሩ ዕይታ ከቀኝ መስመር አድልቶ ወደ ውስጥ በፍጥነት ዕየሮጠ ለመጣው እስራኤል እሸቱ አመቻቶ ያቀበለውን አጥቂው ግብ ጠባቂው ኢድሪስ ወደ ውስጥ ያቀብላል ብሎ በወጣበት አጋጣሚ ወደ ጎል መቶ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቧ በኋላ ወደ ሳጥን በመድረስ የተሻሉ የነበሩት አርባምንጮች 34ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን አምልጦ የገባው ፍቃዱ መኮንን ከግብጠባቂው ሰኢድ ጋር ተገናኝቶ ወጥቶ ጎሉን ስላጠበበ ለእንዳልካቸው መስፍን ሰጥቶት ኳሱን አዙሮ ወደ ጎል የመታው ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ብዙም ሳይቆይ አዞዎቹ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ከባዱ ሙከራ አድርገዋል። ይሁን እንደሻው ከርቀት ያሻገረለትን ኳስ በማሸነፍ በግንባሩ የገጨውን የግቡ ቋሚ ሲመልሰው በድጋሚ ያገኘው አህመድ ሁሴን በማይታመን ሁኔታ አስቆጠረ ሲባል ኳሷን ወደ ሰማይ የሰደዳት ለአርባምንጮች አስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

አዞዎቹ ከየትኛውም አቅጣጫ በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች አደጋ መፍጠራቸውን ሲቀጥሉ ሀዋሳዎች ደግሞ አደጋ ክለል የደረሱ ኳሶችን ማፅዳት ትልቁ ስራቸው ሆኖ አጋመሹን ጎል ሳይቆጠርባቸው 1-0 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ ሆኗል።

ሁለተኛው አጋማሽ 47ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከቀኝ አቅጣጫ ከቅጣት ምት የላከውን በረከት ሳሙኤል በአስገራሚ አክሮባቲክ ሙከራ ሀይቆቹ አድርገው ሲጀምር እንደመጀመርያው አጋመሽ ተመሳሳይ እንቅስቃቃሴ አስመልክቶናል። በተለይ አዞዎቹ የታክቲክም የማጥቃት ባህሪ ያላቸውንም ተጫዋቾች ቀይረው በመስገባት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም የተሳካ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም።

ይልቁንም 65ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። የሀይቆቹ አጥቂ ዓሊ ሱሌማን ከረጀም ርቀት ሳጥን ውስጥ የተጣለለትን ኳሱን በተገቢው መንገድ ተቆጣጥሮ የመጨረሻው ኳሱ ትክክል በለመሆኑ ግብ ጠባቂው ኢድሪስ በቀላሉ ይዞበት ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ ለሀዋሳዎች ዕፎይታ የሚሰጥ ነበር።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ የተጫዋች ቅያሪዎችን ያደረጉት ሀይቆቹ የአዞዎችን ጫና ለማብረድ ሞክረዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ተቀይሮ የገባው ታምራት ኢያሱ በጥሩ ሁኔታ በግንባሩ የገጨው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወጥቶበታል።

ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ሲቀርብ  ሀዋሳዎች ወደ ጥንቃቄው አዘንብለው ሲጨርሱ አዞዎቹ በቆሙ ኳሶች የፈጠሩትን ጫና ወደ ውጤት ሳይቀይሩ ጨዋታው በሀይቆቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።