ሪፖርት | ድራማዊ ትዕይንት በነበረበት ጨዋታ ነብሮቹ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል

ሪፖርት | ድራማዊ ትዕይንት በነበረበት ጨዋታ ነብሮቹ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል

እጅግ አስገራሚ ትዕይንቶችን ባስመለከተን ጨዋታ ነብሮቹ ከመመራት ተነስተው ከ80ኛ ደቂቃ ጀምሮ ባስቆጠሯቸው ሦስት ግቦች 3ለ2 በሆነ ውጤት ወልዋሎን ማሸነፍ ችለዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ሲል በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተጀመረው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር አገናኝቷል። ሀድያ ሆሳዕናዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱበት አሰላለፍ ዳግም ንጉሴ እና በየነ ባንጃን በማሳረፍ በምትካቸው በረከት ወንድሙ እና ብሩክ በየነን ሲያስገቡ በወልዋሎ በኩል ደግሞ አሎሩንለኬ ኦሉዋሴጎን፣ ሃብታሙ ንጉሴ እና ስምዖን ማሩን በማስወጣት በረከት አማረ፣ የአብስራ ሙሉጌታ እና ጋዲሳ መብራቴን አስገብተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

የመጀመሪያዎቹን 15 ያክል ደቂቃዎች ሀድያ ሆሳዕና እጅጉን ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን በቁጥር በዛ ብለው የተቃራኒን ቡድን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መጎብኘት የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ወልዋሎዎች ጥንቃቄን ምርጫቸው በማድረግ የሚሰነዘሩባቸውን የማጥቃት ሙከራዎች በቁጥር በዛ ብለው ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ከጨዋታው ጅማሮ በኋላ ያሉ 15 ደቂቃዎችን መረጋጋት ጎድሏቸው የነበሩት ወልዋሎዎች ያንን በማስተካከል ወደ ጨዋታ የተመለሱ ሲሆን ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ በወልዋሎ በኩል ዳዋ ሆቴሳ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጭ ከተባለበት ኳስ በስተቀር ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው መቅረብ የቻሉት ወልዋሎዎች 53ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ለመግጨት ሲሞክር የነበረው ፉዓድ አዚዝ ሳጥን ውስጥ በሀድያ ተጫዋች ተጎትቶ መውደቁን ተከትሎ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ፉዓድ አዚዝ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

 

የመጀመሪያውን ግብ ማስቆጠራቸው ይበልጥ መነቃቃትን የፈጠረባቸው ወልዋሎዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከተከላካዮች ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ወልዋሎዎችን የማሸነፍ ተስፋ ያለመለመች ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሀድያ ሆሳዕናዎች ከነዚህ ግቦች በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ሙከራ ቢያደርጉም ፊት ለፊት ላይ በሚያሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ምክንያት ያን ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ወልዋሎዎች ሦስተኛ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የጨዋታውን ብልጫ ፍፁም በሆነ መንገድ መቆጣጠር የቻሉ ሲሆን 80ኛው ደቂቃ ላይም የጨዋታውን ግለት የቀየረች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል መድረስ የቻሉ ሲሆን ተቀይሮ የገባው በየነ ባንጃ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ አክርሮ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ በማስቆጠር መነቃቃትን መፍጠር ችሏል።

 

እጅጉን በሚባል ደረጃ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሀድያዎች መደበኛው የጨዋታ ስዓት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው አቻ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 89ኛው ደቂቃ ላይ ተቀባብለው ወደ ግብ በመጠጋት ከሳጥን ጠርዝ ላይ ተቀይሮ የገባው ማሞ አየለ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ መቆጣጠር ባለመቻሉ የመለሰውን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ አድርጓል።

የጨዋታው ጭማሪ ሰዓት ደቂቃዎች ሊያልቁ ሽርፍራፊ ያክል ሰከንዶች ቀርተው የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ለሀድያዎች እጥፍ የሆነ ደስታን የሰጠ ለወልዋሎዎች ደግሞ ተስፋቸውን ገደል የከተተ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 90+5′ ላይ ተመስገን ብርሃኑ በአራት ያክል ተከላካዮች አሾልኮ ያቀበለውን ኳስ ማሞ አየለ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብነት በመቀየር ከቤራዎችን እጅግ ጣፋጭ የሆነ ድልን አቀዳጅቷል።

ይህንንም ተከትሎ የመጨረሻዎቹን 10 ደቂቃዎች ድራማዊ ክስተት ባስመለከተን ጨዋታ ወልዋሎዎች የ2-0 መሪነታቸውን በመገባደጃው ሰዓት ላይ እሳት ለብሰው የመጡትን ነብሮች መቋቋም ተስኗቸው በ10 ደቂቃ ውስጥ በተቆጠረባቸው ሶስት ግቦች ምክንያት በሊጉ የመቆየታቸውን ነገር አጠራጣሪ ያደረገ ሽንፈት አስተናግደዋል ጨዋታውም 3-2 በሆነ ውጤት ከቤራዎች ድል ማድረግ ችለዋል።