እንደ ተጠባቂነቱ ያልነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ 0-0 ተቋጭቷል።
ባለፈው ሳምንት አቻ ከወጡበት አስተላለፍ ንግድ ባንኮች ሱሌማን ሀሚድ እና ካሌብ አማንኩዋህ አሳርፈው እንዳለ ዮሐንስ እና ዘላለም አበበ ለውጠው ለጨዋታው ሲቀርቡ። በአንፃሩ ባህር ዳሮች ከወሳኝ ድላቸው ማግስት መሳይ አገኘው፣ ፍፁም ፍትዓለም፣ ፍሬው ሰለሞን እና ጄሮም ፊሊፕን በቅዱስ ዮሐንስ፣ ግርማ ዲሳሳ፣ ፍፁም አለሙ እና ሙጂብ ቃሲም ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሲያስጀምሩት በጨዋታው እንቅስቃሴ በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው በተለይ በቃኝ መስመር አዲስ ግደይን ትኩረት ያደረጉ ኳስን ማጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢታትሩም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ታይተዋል። አመዛኙን ወደ ራሳቸው የሜዳ ክፍል ተጠግተው ንግድ ባንኮች በሚበላሽባቸው ኳሶች በመንጠቅ አልፎ አልፎ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ፊት ቢሄዱም በተመሳሳይ ባህር ዳሮችም ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
ጨዋታው ከውሃ ዕረፍት መልስ በንፅፅር በሁለቱም በኩል የተመጣጣነ እንቅስቃሴ ቢኖረውም 32ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ፍፁም ያሻገረውን ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ የገጨውን ግብ ጠባቂው ፍሬው በቀላሉ የያዘበት ሙከራ የሚጠቀስ ነው።ንግድ ባንኮች የተሻለ ሆኑ ሲባል በደቂቃዎች ልዮነት ደግሞ የጣና ሞገዶቹ የበላይነት እየወሰዱ ተለዋዋጭ በሆነ እንቅስቃሴ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ቢደረግበትም እጅግ ለጎል የቀረበ አደገኛ ሙከራ ሳንመለከት ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመርያው አጋማሽ ተመሳሳይ በሆነ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ ቅብብሎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ፊት ቢደርሱም የቡድኖች የመከላከል አጥር ጥሩ መሆን እና የተጫዋች የግል ስህተት ታክሎበት ጨዋታውን ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ሙከራ አልባ እንዲሆን አድርጎታል።
በዚህ መልኩ የቀጠለው ጨዋታ ወደ አሰልቺነት አምረቶ ባለበት ሁኔታ ተቀይሮ የገባው ፍሬው ሰለሞን ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ ህክምና እስኪያገኝ ድረስ ጨዋታው እነደዲቋረጥ መሆኑ አንድ ክስተት ነበር። ጨዋታው ከቆመበት ቢቀጥልም ከፊት ያሉት የሁለቱም ቡድኖች አጥቂዎች ተደጋጋሚ በሚሰሩት ስህተት የመጨረሻ ኳሳቸው እየተቋረጠ በቀሩት ደቂቃዎች ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።