ሪፖርት | መድኖች መሪነታቸውን አጠናክረዋል

ሪፖርት | መድኖች መሪነታቸውን አጠናክረዋል

ኢትዮጵያ መድን በአቡበከር ሳኒ ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ መሪነቱን ያሰፋበትን ድል አሳክቷል።

መቐለ 70 እንደርታ በ29ኛው ጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1ለ1 ሲለያዩ ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ ቋሚ አሰላለፍ  የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ሰለሞን ሀብቴን በቦና ዓሊ ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከተማ ሶስት ነጥብ ከሸመተበት ቋሚ አሰላለፍ እንዲሁ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገው ጉዳት ላይ ያለውን መሐመድ አበራን በዳዊት አውላቸው ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ቀን 9:00 ሲል የጀመረው የእለቱ ቀዳሚው መርሐግብር በእንቅስቃሴ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ብልጫ ለመውሰድ በረጃጅም እና በአጫጭር ኳስ ቅብብል ወደ ፊት እየሄዱ ጥረት ያድርጊ እንጂ በሙከራዎች መታጀብ ያልቻሉትን የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ለማሳለፍ ተገደዋል።

በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ከግቡ አቅዳሚ ለትንሽ ከፍ ብሎ ይለፍበት እንጂ ምዓም አናብስቶችን ቀዳሚ ለማድርግ የቀረበ የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ ሙከራ ነበር። ኢትዮ መድን በአንፃራዊነት በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም ወደ ፊት በመሄድ ረገድ ሙሉ በሚባል ደረጃ ብልጫ ተወስዶባቸዋል።

ከደቂቃ ደቂቃ እየቀዘቀዘ የቀጠለው ጨዋታው ከውሃ እረፍት መልስ የባሰ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ አሰልቺ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች አስመልከቷል። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ከፍል መልስ ጨዋታው ተመልሶ ኢትዮጵያ መድን ከመጀመሪያው አንፃር ጠንከር ብለው በመመለስ በቁጥር በርከት ብለው እየገቡ የምዓም አናብስቶችን ተከላካዮች ሲያጨናንቁ አስተውለናል። መቐለ 70 እንደርታው በበኩላቸው እንደመጀመሪያው አጋማሽ መሆን ሳይችሉ ቀርተው በረጃጅም ኳሶች እና በራሳቸው ሜዳ ክፍል እያዘወተሩ ነጥብ የመጋራት ፍላጎት እንዳላቸው አመልካች የሆነ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለመመልከት ችለናል።

በ69ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል የደረሱት ምዓም አናብስቶች በሄኖክ አዱኛ አማካኝነት ግሩም ሙከራ አድርገዋል፤ በተጠቀሰው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ ተጨራርፎ እግሩ ስር የደረሰውን ኳስ ያሬድ ብርሃኑ በተረከዙ ከሳጥን ውጪ ለነበረው ሄኖክ አዱኛ አቃብሎት ጠንከር ያለ ሙከራ ወደ ግብ ቢመታም አቡበከር ኑራ እንዴትም አግዶበታል።

ጨዋታው 72ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ መድኖች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል፤ ከመሃል ሜዳው ለትንሽ ርቆ በግራ መስመር በኩል ሆኖ ሀይደር ሸረፋ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ሲመታት የእለቱ ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ሳይወስኑ ሲቀሩት የእለቱ ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በባንዲራቸው ኳሷ ከመስመር ማለፏን አረጋግጠው መሪ መሆን ችለዋል። ከግቧ መፅድቅ በኋላም የምዓም አናብስቶች የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ተቃውሞ በማስነሳት ክስ ለማስያዝ ከዳኞች ጋር ሲከራከሩ ለመመለከት ችለናል።

ጨዋታው ቀጥሎም መቐለ 70 እንደርታ በመነቃቃት ወደፊት መሄዳቸውን አጠናክረው ቀጥለው የመድኖችን ግብ ለመድፈር አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ተመልክተናል። ሆኖም ግን የመድኖቹ የኋላ መስመር እንደጠበቁት ሊሆንላቸው አልቻለም፤ በዚህም ጠንካራ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ አስተውለናል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃ  የታየው ላይ መድኖች ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ ሙከራ በአለን ካይዋ አማካኝነት አድርገዋል፤ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቧ አግዳሚ ከፍ ብሎ አልፎበታል። ምዓም አናብስቶችም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ፊት እየገቡ ግብ ለማግባት ቢጣጣሩም አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ  ቀርተዋል። በዚህም መድኖች በአቡበከር ሳኒ ብቸኛ ግብ ሶስት ነጥብ ወደ ካዝናቸው አስገብተው ጨዋታው ተጠናቋል።