ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ የሐዋሳ ቆይታቸውን በድል ቋጭተዋል

ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ የሐዋሳ ቆይታቸውን በድል ቋጭተዋል


የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ በሀቢብ ከማል ብቸኛ ግብ አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል።

የ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በወራጅነት አደጋ ስጋት ላይ ያሉትን ሁለት ቡድኖች ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ አገናኝቷል። ድሬዳዋ ከተማዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከ መቐለ  70 እንደርታ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ድልአዲስ ገብሬ እና አቡበከር ወንድሙን በማሳረፍ በምትካቸው አቤል አሰበ እና ዘርዓይ ገብረሥላሴን ሲያስገቡ በተቃራኒው በሐዋሳ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጮች ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ካሌብ በየነ እና እንዳልካቸው መስፍንን በማስገባት አንዱዓለም አስናቀ እና ቡታቃ ሸመናን አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ምሽት 12:00 ሲል በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት የተጀመረው ይህ ጨዋታ ሁለት የመውረድ ስጋት የተደቀነባቸውን ቡድኖች ያገናኘ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን አንዳቸው አሸንፈው ከስጋት በመጠኑም ቢሆን ነፃ ለመሆን እጅግ አስፈላጊ ጨዋታ ነው። ከነጥብ መጋራት እና ከሽንፈት የተመለሱት ሁለቱም ቡድኖች ቀዝቃዛ የሚባል የመጀመሪያ አጋማሽን አስመልክተውናል።

በኳስ ቁጥጥሩ እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ ተቀራራቢ የነበሩ ሲሆን በትንሹም ቢሆን ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስን በመመስረት በመስመር አጥቂዎች ዒላማ ያደረገ የማጥቃት ሙከራ ለማድረግ ሲጥሩ እንዲሁም በተቃራኒ አርባምንጭ ከተማዎች ከተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድልን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ግን በሁለቱም ቡድን በኩል በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተገኝቶ የግብ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ደካማ የሆነ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል። በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያስመለክተን ያለምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን ቡድኖቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ ምንም አይነት የጨዋታ ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ ጨዋታን ለረጅም ደቂቃዎች አስመልክተውናል። ድሬዳዋ ከተማዎች የተጨዋች ለውጥ በማድረግ አቤል አሰበ እና ዘርዓይ ገብረሥላሴን በማስወጣት መስዑድ መሐመድ እና ሀቢብ ከማልን በማስገባት ጨዋታውን በመጠኑም ቢሆን መቆጣጠር ችለዋል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ቅያሪያቸው ፍሬ ያስገኘላቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሁለት ተጨዋቾችን ቀይረው ያስገቡት ድሬዎች በሁለቱም ተቀያሪ ተጫዋቾች አስተዋጽኦ 77ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሐመድ ከግራ መስመር በመሆን ወደ ሳጥን ያቀበለውን ኳስ ሀቢብ ከማል በግራ እግሩ በመምታት ከግቡ አግዳሚ ጋር አጋጭቶ በማስቆጠር ለድሬዎች ጣፋጭ የሆነ ግብን ማስቆጠር ችሏል።

የግቡ መቆጠር መነቃቃትን የፈጠረባቸው አርባምንጮች 80ኛው ደቂቃ ላይ የሜዳው መሃል ክፍል ላይ ከቅጣት ምት በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ታምራት እያሱ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰ ሲሆን በድጋሚ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በድጋሚ ያገኘው ታምራት እያሱ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብጠባቂው አላዛር መርኔ ድንቅ በሆነ ችሎታ እንደምንም ብሎ ወደ ውጭ አውጥቶታል። እነዚህም ለአርባምንጮች እጅጉን ለግብ የቀረቡ አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ።

አርባምንጭ ከተማዎች ውጤቱን ለመቀየር የቻሉትን ያክል ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ጨዋታው በምስራቁ ክለቡ ድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።