ለ45 ያክል ደቂቃዎች በጎደሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት አፄዎቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ መጋራት ችለዋል።
የ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ ምሽት 12 ሰዓት ሲል ፋሲል ከነማን ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገናኝቷል። ፋሲል ከነማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ካስተናገዱበት አሰላለፍ የሶስት ያክል ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ምኞት ደበበ፣ ብሩክ አማኑኤል እና ዳግም አወቀን በማስወጣት በምትካቸው ዮናታን ፍስሃ፣ በረከት ግዛው እና ማርቲን ኪዛን ሲያስገቡ በተቃራኒው ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ እንዳለ ዮሐንስ፣ ኤፍሬም ታምራት እና ብረክ እንዳለን በማሳረፍ ፈቱዲን ጀማል፣ ካሌብ አማንክዋህ እና ሱሌማን ሀሚድን አስገብተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ጨዋታው ሁለት ከውጤት የራቁ ክለቦችን ያገናኘ እንደመሆኑ አንፃር ድል በማድረግ ከራቁት ሶስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት ትልቅ ፉክክር ያስመለክተናል ተብሎ የተጠበቀ ጨዋታ ነበር። የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች በኳስ እና በእንቅስቃሴ ረገድ ንግድ ባንኮች ብልጫን በመውሰድ መጫወት የቻሉ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች በአንፃሩ 15 ያክል ደቂቃዎችን ባለመረጋጋት ውስጥ አሳልፈዋል።
ረጅም ደቂቃዎችን ያለ ምንም ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ እና ማራኪ ያልነበረ ሲሆን 45ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የመጀመሪያ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። ከካሌብ አማንክዋህ መነሻውን ያደረገው እና ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ያገኘው አዲስ ግደይ ግሩም በሆነ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
የአጋማሹ መደበኛ ደቂቃዎች ተጠናቀው በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ የፋሲል ከነማ የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ማርቲን ኪዛ ከዳኞች ጋር በፈጠረው ሰጣገባ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ያገኙትን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ንግድ ባንኮች የፋሲል ተከላካዮችን መስመር ማለፍ ተስኗቸው ተስተውሏል። ይልቁንም በቁጥር የጎደሉ የማይመስሉት ፋሲሎች ጫና ፈጥረው በመጫወት አቻ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ ተከላካይ ካሌብ አማንክዋህ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ወደ ግብነት በመቀየር አፄዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።
የግቡ መቆጠር መነቃቃትን የፈጠረባቸው ንግድ ባንኮች በቁጥር በዛ ብለው ወደ ተጋጣሚ ግብ በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ሲሆን 72ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ በቀኝ መስመር ተነስቶ ሳጥን ውስጥ በመግባት ያቀበለውን ኳስ በዛብህ ካቲሴ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ የመለሰው ሲሆን የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ሳንመን ፒተር ወደ ግብ የመታውን ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ግብ ሳይሆን ቀርቷል።
ደጋግመው ጫና ፈጥረው በመጨወት ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ሚያደርጉት ንግድ ባንኮች እጅጉን ለግብ የቀረበን አስቆጪ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከግራ መስመር አድርጎ የተሻማው ኳስ ሳይመን ፒተር ገጭቶ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ዳንኤል በግንባሩ ቢገጨውም ግብጠባቂው ዮሐንስ እንደምን ብሎ ጨርፎ ወደ ውጭ አውጥቶቷል።
ይህንንም ተከትሎ 45 ያክል ደቂቃዎችን በጎደሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት አፄዎቹ ድንቅ ተጋድሎ በማድረግ ባስቆጠሩት ግብ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።