በትናንቱ የአዳማ ጨዋታ ከፍተኛ በደል ተፈፅሞብኛል ሲል የዓምናው የሊጉ ሻምፒዮን አቤቱታውን አሰምቷል።
የሊጉ 31ኛ ሳምንት ትናንት ዘጠኝ ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በአዳማ ከተማ መካከል የተካሄደው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 2-0 አሸነፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ታዲያ በዚህ ጨዋታ የዳኝነት በደል ደርሶብናል ሲሉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ለሊጉ አክስዮን ማህበር የቴክኒክ ክስ ማቅረባቸውን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዋናነት የዕለቱ ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በ2ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተፈፀመን ጥፋት ሆን ብሎ በማለፍ ቡድኑ ጎል የማግባት ዕድል አምክነዋል። እንዲሁም ሌላ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጠን የሚገባን አጋጣሚ ከሳጥን ውጭ እንደተፈፀመ ተደርጎ ቅጣት ምት እንዲሆን ተደርጓል። 73ኛው ደቂቃ ከጨዋታ ውጭ የሆነ ጎል ተቆጥሮብናል በማለት ቅሬታቸውን በደብዳቤ ለሊጉ አክስዮን ማህበር አስገብተዋል።
በመሆኑ የሊጉ አክስዮን የዕለቱን ጨዋታ የተቀረፀ ቪዲዮዎች በማየት እና የውድድሩን ሂደት በመገምገም አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲሰጠን በአፅኖት እየጠየቅን በቀጣይ የምናደርጋቸውን ውድድሮችን ትኩረት እንድታደርጉልን በማክበር እንጠይቃለን ብለዋል።