ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ የድል ረሀባቸውን አስታግሰዋል

ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ የድል ረሀባቸውን አስታግሰዋል

ሁለቱን ላለመውረድ ትንቅንቅ እያደረጉ የሚገኙ ክለቦችን ባገናኘው መርሃግብር መቐለ 70 እንደርታ 2ለ1 በማሸነፍ የዓመቱ ስምንተኛ ድላቸውን ሲያገኙበት ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው አስራ ሦስተኛውን ሽንፈት አስተናግደዋል።


በሀዋሳ የመጨረሻ ቆይታቸው በመድን ከተረታው ስብስባቸው መቐለዎች ሔኖክ አዱኛ ፣ ቤንጃሚን ኮቴ እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን በማስወጣት ሠለሞን ሀብቴ ፣ ዘረሰናይ ብርሀነ እና ያሬድ ከበደን ሲተኩዋቸው በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብን የተጋሩት ሽረዎች ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ መሐመድ አብዱለጢፍን በክብሮም ብርሀነ ብቻ ለውጠው ቀርበዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በተመራው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ከደርቢው አንዳች ነገርን የፈለጉ ይመስሉ የነበሩት እና ፈጠን ባሉ ሽግግሮች መርጠው የተጫወቱት መቐለዎች ገና በጊዜ በ3ኛው ደቂቃ ጎልን በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። ቦና ዓሊ ከፍ አድርጎ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ያገኘው ያሬድ ብርሀኑ በግንባር አመቻችቶ የሰጠውን ቦና ከግራ በኩል  በግራ እግሩ በመምታት የሞይስ መረብ ላይ  አሳርፏታል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ተመጣጣኝ የሆነ በይበልጥ ግን ወደ ፈጣን ሽግግሮች ያመዘነው ጨዋታ ከመስመር በጥልቀት በሚጫወቱት ሽረዎች በኩል 19ኛ ደቂቃ የአቻነት ጎል ተገኝቶበታል። ብርሀኑ አዳሙ ከግራ የሳጥኑ ክፍል የሰጠውን ኳስ እንደ ወትሮው ሁሉ የመከላከል ስህተት የማያጣው የመቐለ የኋላ ክፍል ዝንጉነት ታክሎበት ፋሲል አስማማው በቀላሉ ጎል በማድረግ ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል።

በመፈራረቅ ብልጫውን ለመያዝ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ባሻገር ዕድሎች በአመርቂ መልኩ ያልነበሩበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ ሁለት አጋጣሚዎች ተፈጥረውበታል። መቐለዎች 37ኛው ደቂቃ ብሩክ ሙሉጌታ ከእጅ ውርወራ ራሱ አስጀምሮ ከያሬድ እግር በድጋሚ  ኳስን ተቀብሎ ወደ ውስጥ ሲያሻግር አሰጋኸኝ ራሱ ላይ ለማስቆጠር ቢቃረብም ሞይስ ጨርፏት ወደ ውጪ ኳሷ ወጥታለች።

መጠነኛ መቀዛቀዝ ይታይባቸው እንጂ ኳስን ሲይዙ የተቃራኒ ሜዳ ላይ በቶሎ የሚደርሱት ሽረዎች እጅግ ያለቀለት አጋጣሚን ቢያገኙም በቀላሉ አምክነውታል። 45ኛው ደቂቃ ሙሉአለም ወደ ቀኝ ለተገኘውን ብርሀኑ ሰጥቶት ተጫዋቹ ተቆጣጥሮ በጥሩ ዕይታ ወደ ቀኝ የሳጥኑ ክፍል የሰጠውን ኳስ ፋሲል አስማማው የግል ጥረቶቹን አክሎ ግብ ጠባቂው ሶፎኒያስ ሰይፈን ጭምር በማለፍ ያደረጋት ሙከራ ዒላማዋን ብቻ መጠበቅ ሳትችል ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድን ሁለቱም ቡድኖች ቢያስመለክቱንም ከፍ ባለ ተነሳሽነት በይበልጥ ለሳጥኑ የተጠጋውን እንቅስቃሴን ያደረጉት መቐለዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ ከቦና የግራ መስመር የተነሳን ኳስ ብሩክ አመቻችቶ ያሬድ ነፃ ሆኖ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ መቶ በተከላካዮች ተደርባ ከተመለሰች ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሠለሞን ሀብቴ ከግራ ያሻገረውን ብሩክ ሙሉጌታ በግንባር ገጭቶ አመቻችቶ ያሬድ ብርሀኑ ዳግመኛ ስህተት ሳይሰራ የግብ ዘቡን ሞይስ ፓዎቴን በተቃራኒው አቅጣጫ አጋድሞ ኳሷን ከመረብ አዋህዶ መቐለን ዳግም መሪ አድርጓል።

ግለቱ ሳይቀንስ ነገር ግን ከሙከራዎች አኳያ መቀዛቀዞች የነበሩት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች መቐለዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ተጨማሪ የግብ ዕድልን በብሩክ ሙሉጌታ ፈጥረው የነፃነት ገብረመድኅን ሸርተቴ ኳሷን ከግብነት የታደገበት ኪሩቤል ከርቀት ያደረጋት ሙከራ ለመቐለ ብርሀኑ አዳሙ በሽረ በኩል በሶፎኒያስ ከተያዘበት አጋጣሚዎች በኋላ ወደ መጨረሻው ደቂቃ ሽረዎች አጥቅተው ቢጫወቱም ጨዋታው ግን  መቐለን ከአምስት ጨዋታዎች መልስ ከድል ያገናኘበትን ውጤት አሳይቶ 2ለ1 ተቋጭቷል።