ሪፖርት | አርባ ምንጭ ከተማ ድል ቀንቶታል

ሪፖርት | አርባ ምንጭ ከተማ ድል ቀንቶታል

አዞዎቹ ከተከታታይ ስምንት ጨዋታዎች በኋላ በአህመድ ሁሴን ሁለት ግቦች የጣና ሞገዶቹን በማሸነፍ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል።

የ32ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ በምሽቱ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማን ከ አርባምንጭ ከተማ ጋር አገናኝቷል። ባሳለፍነው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈትን ያስተናገዱት ባህርዳር ከተማዎች ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ግርማ ዲሳሳ፣ ሄኖክ ይበልጣል እና ወንድወሰን በለጠን በማስወጣት በምትካቸው ወንድሜነህ ደረጀ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ፍፁም ዓለሙን ሲያስገቡ አርባምንጭ ከተማዎች ከዚህ ቀደም ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ታምራት ኢያሱን በ ብሪያን አህብዋ ቀይረው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

በኳሱ ቁጥጥሩ እና በእንቅስቃሴ ረገድ ባህር ዳር ከተማዎች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ግቦችን ማስቆጠሩ ላይ እምብዛም ሁነው ተስተውለዋል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች 36ኛውደቂቃ ላይ ፍሬዘር ካሳ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሁኖ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አጎዶጆ እንደምንም ብሎ ወደ ውጭ አውጥቶታል።

የአጋማሹን የመጨረሻ ደቂቃዎች የጨዋታውን ብልጫ በመውሰድ የማጥቃት ዒላማቸውን የጀመሩት አርባምንጮች 40ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን በግራ መስመር ኳስ ይዞ ወደ ሳጥን በመግባት የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ፔፔ ሳይዶ ግብ ከመሆን ታድጎታል። የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት አዞዎቹ ሳጥን ውስጥ አህመድ ሁሴን ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አህመድ ሁሴን 45+3’ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ማግባታቸው መነሳሳትን የፈጠረባቸው አርባምንጮች ከአንድ ደቂቃ በኋላ ተጨማሪ የግብ ዕድል አግኝተው ብሪያን አብህዋ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ቡታቃ ሸመና ወደ ግብነት የመታውን ኳስ በፔፔ አማካኝነት ግብ ከመሆን ከሽፏል። ይህንንም ተከትሎ በአዞዎቹ 1-0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ባህርዳሮች 52ኛው ደቂቃ ላይ በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግብጠባቂውን ማለፍ ግን አልቻለም። 64ኛው ደቂቃ ላይ በባህር ዳሩ ተጫዋች ወንድሜነህ ደረጄ እና በአርባምንጩ በብሪያን መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የዕለቱ የመሃል ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ የተቃራኒ ተጫዋችን ተማተሃል በማለት ወንድሜነህ ደረጄን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል።

ያገኙትን የቁጥር ብልጫ መጠቀም ያልቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ ከመነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገው እና ወደ ሳጥን የተሻገረው ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘው ተቀይሮ የገባው ታምራት ኢያሱ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር መገናኘት ቢችልም ነገር ግን የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ አውጥቶታል።ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች የባህር ዳርን ተስፋ ያጨለመ ግብ አርባምንጮች ማስቆጠር ችለዋል። 90+2′ ደቂቃ ላይ ቡታቃ ሽመና በጥሩ ዕይታ ያቀበለውን ኳስ አህመድ ሁሴን ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር አዞዎቹን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።

ይህንንም ተከትሎ አዞዎቹ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ባህርዳር ከተማን 2-0 በማሸነፍ ከናፈቃቸው ድል ጋር መታረቅ ችለዋል።