ሪፖርት | አዳማ ከተማ ወሳኝ ሦሰት ነጥብ አሳክቷል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ ወሳኝ ሦሰት ነጥብ አሳክቷል

አዳማ ከተማን ከሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ በረከት ወልደዮሐንስ በራሱ መረብ ላይ ባሳረፋት ግብ ለአዳማ ከተማ ሁለተኛ ተከተታይ ድል በማጎናፀፍ ተጠናቋል።

ረፋድ 3:30 ሲል ጅማሮውን ያደረገው የረፋዱ ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የከተማቸውን ጨዋታዎች በትኩረት እየጠበቁ የሚገኙትን አዳማ ከተማዎችን ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ከተሳናቸው ከሀዲያ ሆሳዕናዎች አገናኝቷል።


አዳማ ከተማ በ31ኛው ሳምንት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲያሸንፉ ከተጠቀሙበት ቋሚ አሰላለፍ የሶስት ተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ሱራፌል አወልን በሙሴ ኪሮስ ፣አብዱልፈታ ሰፋን በነቢል ኑሪ እና ስንታየሁ መንግስቱን በቢኒያም ዓይተን ተክተው ሲቀርቡ ለዲያ ሆሳዕናዎች ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አቻ ሲለያዩ ይዘው ከቀረቡት ቋሚ አሰላለፍ የሶስት ተጫዋች ለውጥ አድርገው ቃለአብ ውብሸት፣ ናትናኤል ሞገስ እና ብሩክ ማርቆስን በማሳረፍ በምትካቸው ሄኖክ አርፊጮ ፣ሰመረ ሀፍተይ እና አስጨናቂ ፀጋዬን ይዘው ቀርበዋል።

ጨዋታው እንደጀመረ ቡድኖቹ ቀዳሚ ለመሆን ወደፊት ሲሮጡ ያስተዋልን ቢሆን ሀዲያ ሆሳዕናዎች አደገኛ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ፤ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በረከት ወልደዩሐንስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች እንዴትም ተረባርበው አውጥተውባቸዋል።

አዳማ ከተማዎችም በበኩላቸው በ8 ደቂቃ ላይ በደንብ ወደ ግብ የተጠጉበትን አስቆጪ አጋጣሚ ፈጥረዋል፤ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ቢኒያም አይተን በፍጥነት ደርሶ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም በየነ ባንጃ እንዴትም ሮጦ ደርሶ ያገደበት አጋጣሚ አዳማዎች መሪ ለማድረግ የቀረበ አስቆጪው አጋጣሚ ነበር። እንዲሁም 17ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ኳስ ይዘው የገቡት አዳማዎች በነቢል ኑሪ አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ ኢላማውን ሳየጠብቅ ይቅር እንጂ ሌላኛው አደገኛ ሙከራቸው ነበር።

በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል እየደረሱ የሰነበቱት አዳማ ከተማዎች በ36ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። አቤነዜር ሲሳይ ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ ከተከላካዮች መካከል የሰነጠቀውን ኳስ ቻላቸው መንበሩ ደርሶ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ቢኒያም አይተን ጨርፎት ከኋላው ሲሮጥ በነበረው በሀዲያ ተከላካይ በረከት ወልደዩሐንስ ላይ ኳሱ ተነካክቶ በእራሳቸው ግብ ላይ ጎሉ ተቆጥሮ አዳማ ከተማን መሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የአጋማሹ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ አዳማ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ አከታትለው ሙከራ አድርገዋል ፤ 47ኛው ደቂቃ  ላይ ነቢል ኑሪ የቆመ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው ሲያግድባቸው እንዲሁም ነቢል ኑሪ እና ሙሴ ኪሮስ በአንድ ለአንድ ቅብልል ኳስ ይዘው ገብተው ቢኒያም አይተን ወደ ግብ የመታውን ኳስ በድጋሚ ስንታየሁ ታምራት በቀላሉ አግዶባቸዋል። አጋማሹም በአዳማ ከተማ ግብ ሙከራ በላይነት እና በአንድ ግብ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ተመልሶ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጠንከር ብለው ተመልሰው ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ኳስ መስርተው በአጫጭር ቅብብል የተጋጣሚያቸውን ሜዳ ክፍል ሲደርሱ አስተውለናል። አዳማ ከተማዎችም በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት እየሄዱ መሪነታቸውን ለማጠናከር ሲጥሩ ብናስተውልም ጨዋታው ወደ ስልሳዎቹ ደቂቃ እስኪገባ ጠንካራ ሙከራ በሁለቱም ቡድኖች መካከል አልተመለከትንም። ሆኖም ግን በሁለቱም ቡድኖች መካከል የግብ ማግባት ፍላጎት በመኖሩ ቶሎ ቶሎ ከሳጥን ሳጥን ሲደርሱ አስተውለናል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በሙከራዎች መታጀብ ያልቻለው ሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ፊት በመሄድ እንቅስቃሴ አንፃር ጥሩ ፉክክር እያስመለከተን ቀጥሏል። ቡድኖቹም አንዱ ላለመሸነፍ አንዱ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ የሆነ ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት በሚያደርጉት ፍልሚያ የጨዋታው ግለቱ ከደቂቃ ደቂቃ እየጨመረ ሄዷል።

ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች እያስመለከተ በቀጠለው በዚህ ጨዋታ ወደፊት ሄደው የሚፈጥሩት የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በአግባቡ ለመጠቀም ሲቸገሩ አስተውለናል። እንዲሁም አዳማ ከተማዎች አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ ብልጫ ነበራቸው። ጨዋታው ሳቢ የሚባል እንቅስቃሴ እየስመለከተ ቢቀጥልም ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አደገኛ የግብ ማግባት ሙከራ እንዲሁም አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ ሳይፈጠር ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ዘልቋል።

ጨዋታው ወደ መገባደጃው ሲቃረብ ከቤራዎች ከሽንፈት ለመታደግ ኳስ ይዘው እየገቡ የአዳማ ከተማዎችን ተከላካዮች የፈተኑ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ተመልክተናል። ሆኖም ግን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ ስንቅ የሆነውን እና እጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጠንከር ባለ ጥንቃቄ ሲጫወቱ የነበሩት አዳማ ከተማዎች የሚቀመሱ አልሆኑላቸውም። ይልቁንስ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።

ነጥቡ ይበልጥ ያስፈልጋቸው የነበሩት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ሄድ መለስ እያሉ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢጣጣሩም በአማዛኙ በእራሳቸው ሜዳ ክፍል ላይ ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ ተመልክተናል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳያስመለክተን በረከት ወልደዩሐንስ በራሱ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ  ለአዳማ ከተማዎች ወሳኝ ሶስት ነጥብ በማስገኘች ተቋጭቷል።