ኢትዮጵያ ቡና ከሊጉ ከወረደው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ያለ ጎል ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ከመሪው መድን ጋር ያላቸውን ነጥብ ማጥበብ ሳይችል ቀርተዋል።
ከሊጉ የወረዱት ወልዋሎዎች ከቀናት በፊት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት ጨዋታቸው ዮናስ ገረመውን በሠለሞን ገመቹ ብቻ ሲቀይሩ ኢትዮጵያ መድን ላይ ወሳኝ ድል በተቀናጁት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ግን ምንም ቅያሪ ሳይኖራቸው ለጨዋታው ቀርበዋል።
ወልዋሎዎች ከሊጉ መውረዳቸው ቢረጋገጥም ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመጨረስ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ በይበልጥ ለማሳመር ይረዳቸው ዘንድ ያደረጉት የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ መርሀ-ግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ከፉክክር የዘለለ ጠጠር ባሉ ሙከራዎች መድመቅ የተሳነው ነበር። ተመጣጣኝ አጀማመር ቢኖረውም በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ ከመስመር መነሳትን መርጠው መጫወት የቻሉት ወልዋሎዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራን ሰንዝረዋል።
ሚካኤል ኪዳኔ ከመሐል ሜዳው በረጅሙ ወደ ቀኝ የተጣለለትን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ በግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም ተመልሳ ወደ ግቡ እያመራች ያለች ኳስን በፍቃዱ ዓለማየሁ ደርሶ ከጎልነት የታደጋት አጋጣሚ ምንአልባትም በአጋማሹ የጠራችዋ ሙከራም ሆናለች። ከወትሮው እንቅስቃሴያቸው በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ቢሉም ከተለመደው የንክኪ አጨዋወት በተጨማሪ ከመስመር ኮንኮኒ ሀፊዝን የሚፈልጉ ተሻጋሪ ኳሶችን ሲጠቀሙ ቢስተዋልም ቡድኑ ላይ ይንፀባረቅ የነበረው አለመረጋጋት በቀላሉ የሚገኙ ዕድሎችን እንዳይጠቀሙ አግዷቸው ታዝበናል።
አማኑኤል በጥልቅ እንቅስቃሴ ረጂብ በሚሻገር ኳሶች አንዳች ነገርን ፈልገው በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የተጫወቱት ቡናማዎች 22ኛው ደቂቃ ረጂብ አሻምቶ ኮንኮኒ በግንባር የገጨው እና አማኑኤል በተመሳሳይ ለኮንኮኒ ሰጥቶ የተጫዋቹ ሙከራ በግብ ዘቡ ናትናኤል ኪዳኔ የተመከተው አጋጣሚ ሊጠቀሱ የሚችሉ ቢሆኑም ጥድፊያዎች በጥቅሉ በቡድኑ ላይ መታየቱ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል ናትናኤል ሠለሞን ለወልዋሎ አማኑኤል አድማሱ ለኢትዮጵያ ቡና ከሰነዘሯቸው ደካማ ሙከራ መልስ አጋማሹ ተገባዷል።
ከዕረፍት ቡናማዎቹ ስንታየሁ ዋለጪን በሚኪያስ ፀጋዬ ተክተው ከተመለሱ በኋላ ብልጫን ቢይዙም እንደነበራቸው የመጨረሻው ሜዳ የበላይነት ግን በጎል ሙከራዎች መድመቅ ያልቻሉበት ነበር። ጥንቃቄ ላይ አመዝነው የኋላ ክፍላቸውን በአመዛኙ ሽፋን በመስጠት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረትን አድርገዋል። በ54ኛው ደቂቃ ዲቫይን ወደ ሳጥን ሰንጥቆ የሰጠውን ኳስ የወልዋሎ ግብ ጠባቂ ናትናኤል ኪዳኔ የጊዜ አጠበበቅ ስህተት ታክሎበት አማኑኤል አድማሱ ያገኛትን ኳስ ሞክሮ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ታካ የወጣችበት ለቡናማዎቹ አስቆጪዋ ዕድል ነበረች።
እንደነበራቸው የእንቅስቃሴ የበላይነት በሙከራ የተቀዛቀዙት ቡናማዎቹ በ69ኛው ደቂቃ ረጂብ ሚፍታ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ጎል የላከትን ኳስ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ኪዳኔ ያወጣው እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኪሩቤል ደሳለኝ ከቅጣት መቶ የውጪው መረብ ኳሷ ነክታ የወጣችበት እንዲሁም 85ኛው ደቂቃ ሚኪያስ ፀጋዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ናትናኤል ኪዳኔ በጥሩ ቅልጥፍና ካዳናት ኳስ በኋላ በመከላከሉ ጥብቅ የነበሩት ወልዋሎዎች ፍፁም ብልጫ ቢወሰድባቸው ጨዋታ በመጨረሻም 0ለ0 ተቋጭቷል። ውጤቱም ኢትዮጵያ ቡና ከመሪው መድን ጋር ነጥቡን የሚያጠብበትን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።