ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የጦና ንቦችን 1-0 በማሸነፍ ከአምስት ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል::
የ32ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በምሽቱ መርሐግብር ወላይታ ድቻን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል። ወላይታ ድቻዎች ከመቻል ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አዛሪያስ አቤል፣ ናትናኤል ናሴሮ፣ ያሬድ ዳርዛ፣አብነት ደምሴ፣ብዙአየሁ ሰይፉ እና ካርሎስ ዳምጠውን በማሳረፍ በምትካቸው መልካሙ ቦጋለ፣ ፍፁም ግርማ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ ሙሉቀን አዲሱ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና መሳይ ሰለሞንን ሲያስገቡ በተቃራኒው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ አብዱልዓዚዝ አማን እና እዮብ ገ/ማርያምን በማስወጣት በምትካቸው አሸናፊ ጥሩነህ እና ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስን በማስገባት ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው እንደመገናኘታቸው አንፃር አሸንፎ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆነ አንፃር ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል። ጅማሮው ላይ ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሲሆን በሙከራ ረገድ ድቻዎች ቀዳሚ ነበሩ 6ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የግብ ክልል መስርተው ያመጡትን ኳስ መሳይ ሰለሞን ከሳጥን ውጭ ሁኖ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው እንደምንም ብሎ አውጥቶበታል።
42ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ጠርዝ ላይ ሽመክት ጉግሳ ለማሻማት በሚመስል መልኩ የመታውን ኳስ ወደ ግብ አምርቶ ግብ ጠባቂው እንደምንም ተንጠራርቶ በአግዳሚው አናት አስወጥቷል።የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ በአጋማሹ ደካማ የነበሩት ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ እምብዛም ሙከራዎችን ሳያሳየን የቆየ ቢሆንሞ 64ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገ እና ወደ ሳጥን የተሻረገውን ኳስ ቴዎድሮስ ታፈሰ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ኤሌክትሪኮችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ወላይታ ድቻዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ነገር ግን ጥንቃቄን የተሞላበትን አጨዋወት ምርጫቸው በማድረግ መከላከሉ ላይ በዛ ብለው ኤሌክትሪኮች የገነቡትን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው ጨዋታው ተጠናቋል።
ይህንንም ተከትሎ የመውረድ ስጋት ውስጥ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ወላይታ ድቻን 1-0 በማሸነፍ በመጠኑም ቢሆን እፎይ ያሉበትን ድል አስመዝግበዋል።