ኢትዮጵያ መድን በትናንትናው ዕለት ኢትዮጵያ ቡና በፃፈው ደብዳቤ ዙርያ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እና ይህ ካልሆነ አቤቱታው ወደ የሚመለከተው ክፍል ለማቅረብ የሚገደድ መሆኑን ገልጿል።
ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና በደብዳቤ ያቀረበው አቤቱታ በማህበራዊ መገናኛ መመልከቱን ከገለፀ በኋላ አቤቱታው በጥቅሉ ተገቢ ያልሆነና ማስረጃ የሌለው መሆኑ በመግለፅ ክለቡን እና በሀገሪቱ ውስጥ በቅንንትና በታማኝነት ህብረተሰቡን እያገለገለ ያለውን ድርጅቱን ስም፣ ክብር እና ዝና ከማጠልሸት ሌላ በጨዋታው ከሥነ ምግባር የራቁ ምንም ተግባር እንዳልተፈፀሙ ገልጿል።
ክለቡ ጨምሮም አቤቱታ አቅራቢው ኢትዮጵያ ቡና ድርጅቱ የሀገሪቱን ሕዝብ በቅርብ የሚከታተለውንና የሚያዘወትረውን እግር ኳስ ስፖርት በማሳደግ እና በማስፈን በኩል የበኩሉን እገዛ ሲያደርግ የቆየውን እና የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ እየሰጠ ያለውን ተቋም ለሀገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ተግባራት ፈፅሟል ብሎ ስም ከማጥፋት ሌላ ተግባራቱን ዘርዝሮ እንዳላስቀመጠም ጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ ከዚህ በፊት ሀገሪቱን ወክሎ በካፍ ካፕ አፍሪካ ክለቦች ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን በማጠናቀቅ የሀገሪቱን በእግር ኳሱ ያለችበትን ደረጃ ከፍ በማድረግ ረገድ አንድ ጉልህ ተግባር መፈፀሙን በመግለፅ በዘንድሮው ውድድር በሰፊ የነጥብ ልዮነት ሊጉን በአንደኝነት እየመራ የዘለቀ መሆኑ ገልፆ ክለቡ ከእግር ኳስ ሥነ ምግባር እጅግ የራቀ ተግባር ፈፅሟል ብሎ የተጫዋቾቹን ፣ የአሰልጣኝ ቡድኑን እና ተቋሙን ስም ገፅታ ማበላሸት ትክክል አይደለም ብሎ እንደሚያምንም አስረድቷል።