ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማዎች ወሳኝ ድል አሳክተዋል

ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማዎች ወሳኝ ድል አሳክተዋል

የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ከመመራት ተነስተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-1 በማሸነፍ ተከታታይ ሦስተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

የ32ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ 2-0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ኪቲካ ጅማ እና ናትናኤል ዳንኤልን በማስወጣት ተስፋዬ ታምራት እና ብሩክ እንዳለን ሲያስገቡ በተቃራኒው ባህርዳር ከተማን 2-1 በማሸነፍ ከድል የተመለሱት ድሬዎች ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በሁለቱም ቡድን መጠነኛ እና ተቀራራቢ የኳስ ቁጥጥር በነበረው በምሽቱ ጨዋታ ንግድ ባንኮች በጨዋታው ጅማሬ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይአዲስ ግደይ እና ዘላለም አበበ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን በመጠጋት ዘላለም አበበ ያሾለከለትን ኳስ ቢንያም ካሳሁን ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋለ ድሬዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉ ሲሆን 31ኛው ደቂቃ ላይ ድካማቸው ፍሬ ያፈራበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከሜዳው የግራ ክፍል አብዱልሰላም የሱፍ ያሻገረውን ኳስ ዮሐንስ ደረጀ ወደ ግብነት ቀይሮ ድሬዎችን አቻ አድርጓል።

የግቡ መቆጠር መነሰሳትን የፈጠረባቸው ድሬዎች የመጀመሪያ ግባቸውን ካስቆጠሩ ከሁለት ደቂቃ በኋላ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ኢስማኤል አብዱል ጋኒዩ በግንባሩ በመግጨት ከመመራት ወደ መሪ መሆን የተሸጋገሩበትን ግብ አስቆጥሯል። የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ግን ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው የመጀመሪያው አጋማሽ በድሬዳዋ መሪነት ተጠናቋል::

ከዕረፍት መልስ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ሁለቱም ቡድኖች ያለ ሙከራ ያስመለከቱን ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች መከላከልን ምርጫቸው በማድረግ አልፎ አልፎ የሚያስጥሏቸውን ኳሶች ይዘው ወደ ፊት በመሄድ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲግሩ ተስተውሏል። በተመሳሳይ ንግድ ባንኮች የኳስ ቁጥጥር እና እንቅስቃሴ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የግብ ዕድሎችነ በመፍጠር ረገድ ደካማ የሆነ እንቅስቃሴን አስመልክተውናል።

በተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ንግድ ባንኮች በድሬዳዋ ከተማ የተቀናጀ የመከላከል ስራ ግብ ማግኘት ተስኗቸው ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል።