ሀዋሳ ከተማ መቻልን 3ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ ላለመውረድ ከሚደረገው ፉክክር በይበልጥ ያራቃቸውን ወሳኝ ሦስት ነጥብን አግኝተዋል።
መቻል ከወላይታ ድቻ ጋር ሀዋሳ ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር ከቀናት በፊት በተመሳሳይ 1ለ1 ካጠናቀቁት ጨዋታ መቻል በአራቱ ሀዋሳ ደግሞ በሁለቱ ላይ ለውጥን አድርገዋል። ለሀገራዊ ጥሪ ወደ ዮጋንዳ ያመራው አሊዮንዚ ናፊያንን በውብሸት ጭላሎ ፣ ዳዊት ማሞን በግሩም ሐጎስ ፣ አማኑኤል ዮሐንስን በበሐይሉ ግርማ እና አቤል ነጋሽን በዮሴፍ ታረቀኝ መቻሎች ሲተኩ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ሠለሞን ወዴሳን በበፍቃደስላሴ ደሳለኝ ፣ እስራኤል እሸቱን ደግሞ በቸርነት አውሽ ለውጠው ቀርበዋል።
በፌድራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ በተመራው ጨዋታ ሀዋሳዎች በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በወሰዱት የእንቅስቃሴ ብልጫ ጎልን ያስቆጠሩበት ነበር። 5ኛው ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ ቢኒያም በላይ በግሩም ዕይታ ወደ ግራ የጣለውን ኳስ ዓሊ ሱለይማን ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ በድንቅ አጨራረስ መረብ ላይ በማሳረፍ ሐይቆቹን መሪ አድርጓል።
ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በሦስቱም የማጥቂያ ቦታዎች ላይ በወሰዷቸው የበላይነት ደጋግመው ሦስተኛው ሜዳ ላይ ሲደርሱ የሚታዩት መቻሎች እንደነበራቸው ከፍ ያለ እንቅስቃሴ አኳያ ማጥቃቶቻቸው በጥድፊያዎች የተሞሉ ነበሩ።
በ10ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከማዕዘን ያሻማውን ሽመልስ በግንባር ገጭቶ በግቡ አግዳሚ ዒላማዋን ሳትጠብቅ የወጣችበት እና ከአስር ደቂቃ በኋላም ከቀኝ ዓለምብርሀን አሻግሮለት ሽመልስ ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ሲሞክር በተከላካይ ተደርባ ስተመለስ በሐይሉ ግርማ ከሳጥን ውጪ የመጣችለት ኳስ ቢመታም ፂሆን መርዕድ ሳይቸገር በቀላሉተቆጣጥሮበታል። በእንቅስቃሴ ቢበለጡም ዓሊ ሱለይማን ላይ ያተኮሩ ረጃጅም ኳሶች ሲጠቀሙ የተስተዋሉት ሀዋሳዎች በ24ኛው ደቂቃ በተጠቀሰው አጨዋወት ዓሊ ከቀኝ ሳጥኑ ያገኛትን ዕድል በግቡ አግዳሚ በኩል ታካ ወጥታበታለች።
ከሚደረጉ የኳስ ንክኪዎች በቀር በጠሩ የግብ ዕድሎች መድመቅ የተሳነው ጨዋታ 40ኛው ደቂቃ ላይ የመቻሉ ተከላካይ አስቻለው ታመነ ከዕለቱ የመሐል ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ጋር በተደጋጋሚ ያደርግ በነበረው ሰጣ ገባ በመጨረሻም በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወገድ አድርጎታል።
45ኛው ደቂቃ መቻሎች ወደ ጨዋታ የምትመልሳቸውን አጋጣሚ አግኝተው ነበር በረከት ሳሙኤል ወደኋላ ለግብ ዘቡ ፂሆን መርዕድ የሰጠውን ኳስ ባሳየው መዘናጋት ሽመልስ ነጥቆት የነበረ ቢሆንም የራሱን ስህተት ያረመው ፂሆን ኳሷን ከያዛባ በኋላ ጨዋታውም ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ መቻሎች በሐይሉ ግርማ እና ዮሴፍ ታረቀኝን በአቤል ነጋሽ እና ምንይሉ ወንድሙ ሲተኩ ሀዋሳዎች ደግሞ ቸርነት አውሽን በአቤኔዘር ዮሐንስ ቀይረው ተመልሰዋል። የቁጥር ብልጫን በመያዝ በይበልጥ ከአጋማሹ መጀመር አንስቶ ወደ ፊት ተስበው መንቀሳቀስ የቻሉት ሀዋሳዎች 49ኛው ደቂቃ ዓሊ የሰጠውን ኳስ አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ውጪ ለተገኘው ተባረክ ሄፋሞ ሰጥቶት አጥቂውም አክርሮ በመምታት የውብሸት ጭላሎ መረብ ላይ በማስቀመጥ የቡድኑን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ካደረገ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ሦስተኛ ግባቸውን በግሩም አጨራረስ አስቆጥረዋል።
ከአማኑኤል ጎበና ያገኛትን ኳስ ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ሦስት ተጫዋቾችን ጭምር በማለፍ በድንቅ አጨራረስ አቅሙን ያሳየበትን ጎልን ለቡድኑ አክሏል። ሦስት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ ተጫዋች በመቀየር መጠነኛ መነቃቃት የነበራቸው መቻሎች ምንይሉ ካደረጋት ሙከራቸው መልስ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረዋል። በረከት ደስታ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ወደ ውስጥ ሲያሻማ ፊልሞን በግንባር ገጭቶ ብሩክ ታደለ በእጅ የነካውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ወደ ጎልነት ቀይሮ ጨዋታው ወደ 3ለ1 ተሸጋግሯል።
ሀዋሳዎች በ73ኛው ደቂቃ ከግራ ዓሊ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ከጠጣብ አንግል የሞከረው ውብሸት ጭላሎም የመከተበትት መቻሎች በበኩላቸው በዳንኤል ዳርጌ እና አቤል ነጋሽ በኩል በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሙከራዎቹ እምብዛም አስፈሪ አልነበሩም። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ በረከት ሳሙኤል ከቅጣት ምት ከርቀት ካደረጋት አደገኛ ሙከራ እና ውብሸት ጭላሎ እንደምንም ከያዛት ኳስ በኋላ ጨዋታው በሀዋሳ የ3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ሀዋሳን ከወራጅ ስጋት በይበልጥ ያራቀውን ወሳኝ ውጤት የያዘበት ሆኗል።