አስቀድመው የሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት መድኖች መቻልን 2ለ0 በማሸነፍ ነጥባቸውን ወደ 67 ከፍ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ መድኖች በ33ኛው ጨዋታ ሳምንት ከፈረሰኞቹ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ይዘው ከገቡት የመጀመሪያ ቋሚ አሰላለፍ የአራት ተጫዋች ለውጦች አድርገው፤ በረከት ካሌብን በረመዳን ሁሴን፣ ሐይደር ሸሪፋን በምንተስኖት አዳነ፣ ዳዊት ተፈራን በዳዊት ተፈራ እና አብዲሳ ጀማልን በአለን ካይዋ ተክተው ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 1ለ1 አቻ ሲለያዩ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ ውብሸት ጭላሎ፣ ዩሐንስ መንግሥቱ እና አቤል ነጋሽን አሳርፈው በምትካቸው ምንታምር መለሰ፣ አማኑኤል ዩሐንስ እና ዩሴፍ ታረቀኝን ይዘው ግብተዋል።
አስቀደመው የ2017 ዓም የሊጉ ሻምፒዮን መሆናቸውን ያረጋገጡትን ኢትዮጵያ መድንን በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ እራሳቸውን ካስቀመጡት ከመቻሎች ጋር ያገናኘው የእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መቻሎች ቶሎ የግብ እድል ፈጥረው ወደ ጨዋታው ለመግባት ኳስ ተቆጣጥረው ሳጥን ውስጥ በመድረስ ጫና ለማሳደር ጥረት ያደረጉበትን አስር ደቂቃዎች ሲያስመለክተን፤ መድኖችን በአንፃራዊነት የተሳካ የኳስ ቅብብል ማድረግ ያልቻሉበትን ደቂቃዎች አስመልክተውናል።
ወደ ፊት በመሄድ አኳያ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች በ11ኛው ደቂቃ ላይ በዳዊት ማሞ አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ ሲጠቀስ በመስመር በኩል ኳስ ይዘው ገብተው ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ አሻግሮ ከግቡ ቋሚ ብረት ለጥቂች ርቆ ውጥቶባቸው በሁለት ደቂቃ ልዩነት በ13ኛው ደቂቃ እንዲሁ በመስመር በኩል ኳስ ይዘው ገብቶ የሳጥን ጠርዝ ላይ ሆኖ ዮሴፍ ታረቀኝ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ የተቆጣጠረባቸው ሌላኛው ሙከራ ይታወሳል።
መጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ወደ ፊት በመሄድ ረገድ ብሎም በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶባቸው የሰነበቱት መድኖች በ19ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ በዚህ ደቂቃ ከእራሳተው ሜዳ ክፍል በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ረመዳን የሱፍ ደርሶ ከጀርባው ለነበረው ዳዊት አውላቸው ወደ ኋላ መልሶ አሻግሮለት ቀጥታ ወደ ግብ ጠጠር ያለ ኳስ መጥቶ ግብ ጠባቂው ያገደባቸው አደገኛው ሙከራ ይጠቀሳል።
ኢላማቸውን የተጠበቁ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች የአጋማሹ አካፋይ ላይ ጠንካራ ሙከራ በቆመ ኳስ አድርገዋል፤22ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ኳስ ይዘው ሲገቡ ሺመልስ በቀለ ላይ ረመዳን ሁሴን በሰራው ጥፋት ቅጣት ምት የሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ አግኝተው ዮሴፍ ታረቀኝ ቅጣት ምቱን ወደ ግብ መጥቶ አቡበከር ኑራ እንዴትም ጨርፎ ከግቡ ቋሚ ጋር ተጋግዘው ኳሱን ወደ ውጪ ያውጡት እንጂ ቀዳሚ ለመሆን በደንብ የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር። ከውሃ እረፍት መልስ ጠንከር የተመለሱት መድኖች ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ሙከራዎች አድርገዋል። ከሙከራዎች መካከል 36ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ረመዳን የሱፍ በግንባሩ ገጭቶ ለአለን ካይዋ አሻግሮለት በግንባሩ ወደ ግብ ሲያሻግር ግሩም ሀጎስ መልሶባቸው እራሱን ኳስ ሳጥን ውስጥ ዋንጫ ቱት ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረባቸው ለግብ የቀረበ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።
ተወስዶባቸው የነበረውን የጨዋታ ብልጫ ወደ አጋማሹ መገባደጃ አከባቢ ቀልብሰው ኳስ ተቆጣጥረው የጨዋታ በላይነትን የወሰዱት መድኖች ከተደጋጋሚ የግብ ማግባት እንቅስቃሴ በኋላ መሪ መሎን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ማጥቃት እንቅስቃሴ በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ ግብተው ዳዊት አውላቸው ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለነበረው ወገኔ ገዛኸኝ ኳሱን አሻግሮለት ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ግብነት ቀይሮ የግብ ብልጫ እንዲወስዱ አድርጓቸው በመሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ስቀጥል ቡድኖቹ እየተፈራረቁ የኳስ ብልጫ እየወሰዱ ተጨማሪ ግቦችን ለማስመልከት እጅጉን እየቀረቡ የቀጠሉ ሲሆን መቻሎች የያዙትን ነጥብ አስተማማኝ ባለመሆኑ ከሽንፈት ሊታደጋቸው የሚችል የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በቁጥር በርከት ብለው እየገቡ የሻምፒዮኖቹን ተከላካይ መስመር እየፈተኑ ጨዋታው ወደ ስልሳዎቹ ደቂቃዎች ደርሷል። የመቻሎችን ጫና እየተቆጣጠሩ በረጃጅም ኳሶች በመልሶ ማጥቃት እየገቡ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት መድኖች 68ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ በአለን ካይዋ አማካኝነት አስቆጥረዋል። በቀኝ መስመር በኩል በረጅሚ የተጣለውን ኳስ በረከት ካሌብ በፍጠንት ደርሶ ወደ ሳጥን አሻግሮ አለን ካይዋ በቀላሉ ጭርፎ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን ማጠናከር ችሏል።
መቻሎች ከእራሳቸው ሜዳ ክፍል ወጥተው በሙሉ ኃይላቸው ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ግብ ፍለጋ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ ያዘውትሩበትን ሁለተኛውን አጋማሽ ቢያሳልፉም ይዘው የሚገቡትን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት ለመቀየር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ንቁ ሆኖ ኳሶችን እያመከን በዋለው በመድኖች ተከላካይ መስመር እየተቆራረጠባቸው ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ለመዝለቅ ተገዷል። የሁለት የግብ ብልጫ የወሰዱት ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው በተረጋጋ አጨዋወት ኳስ መስርተው እየተጫወቱ አለፎ አልፎም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በአጫጭር ኳስ ቅብብል ሲገቡ አስተውለናል።
ተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን ያስቀጠሉት መድኖች 86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው አብዲሳ ጀማል አማካኝነት ሶስተኛ ግብ ለመሆን ፍፁም የቀረበ አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ሻምፒዮን በተለይ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲያመራ ኳስ ተቆጣጥረው ወደ ራሳቸው ሜዳ እየመለሱ ደቂቃውን ወደመጨረስ የገቡበትን የጨዋታ ክፍለጊዜ ሲያሳልፉ ተመልክተናል።
መቻሎችም በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የቀረቡበትን ሙከራ በዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት አድርገው የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። እንዲሁም ጭማሪ ደቂቃ ላይ ያደረጉትን ሙከራ ጥሩ ኳሶችን ሲያበላሽባቸው የነበረው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ መልሶባቸው ጨዋታው ለወድድሩ አመቱ አሸናፊዎች ሁለት ንፁህ ግብ ከሙሉ ሶስት ነጥብ ጋር በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጨናቀቅ በኋላ አሰልጣኞቹ አሰተያየት የሰጡ ሲሆን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የዋንጫ ክብር ይዞ መልሶ መሸነፍ ደስታውን የተቆራረጠ እንዳያደርግባቸው ትኩረት እንዳደረጉ ተናግረው በያዙባቸውን ቡድኖች በፍላጎት፣ በጥረት፣ በአንድነት እና በፍቅር አስተሳስረው ሻምፒዮን እንዲሆኑ እንዳደረጉ ገልፀው አሸናፊ በሆነባቸው ባለፉት ጊዜያት ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ተናንቀው ዋንጫውን መውሰዳቸውን አውሰው ዘንድሮ ቀሪ ጨዋታዎች እያሉ ይሄን ማሳካታቸው ለየት ያለ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በበኩላቸው በጨዋታው በልጠው እንዳሸነፏቸው ማመን እንዳለባቸው ገልፀው ያቀዱትን አጨዋወት እንዳልተጫወቱ እና ተጋጣሚዎቻቸው ሻምፒዮን ከመሆናቸው አንፃር በፍላጎት መብለጣቸው አንዱ ችግር እንደሆነባቸው አንስተዋል።