ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከነማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከነማ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጨዋታ ሳምንቱ በጉጉት ከሚጠበቁ መርሐግብሮች ቀዳሚው ነው፤ ቡድኖቹ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ወሳኝ ነጥብ ማስመዝገብ በሚገባቸው ወቅት ላይ መገናኘታቸውም ፍልሚያውን ተጠባቂ ያደርገዋል።

በጨዋታ ሳምንቱ እጅግ ተጠባቂ ከሆኑ መርሐግብሮች አንዱ የሆነው ይህ ፍልሚያ በወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ለሚፋለሙት ሁለቱም ቡድኖች ከፍ ያለ ትርጉም አለው። ሁለቱም ቡድኖች በወራጅ ቀጠናው መውጫ ላይ ከቆሙት መቐለ እና አዳማ በተመሳሳይ ነጥብ ላይ እንደመገኘታቸውም ከጨዋታው ይዘውት የሚወጡትን ነጥብ ለመትረፍ በሚያደርጉት ትግል ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።

በሰላሳ ስምንት ነጥብ ከነገው ተጋጣሚው በግብ ክፍያ በልጦ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከሽንፈት ቢርቅም በመርሐግብሮቹ ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ማሳካት የቻለው ስድስቱን ብቻ ነው። ቡድኑ ከነገው ተጋጣሚው አንፃር ሲታይ በቅርብ ሳምንታት የተሻሉ ነጥቦች መሰብሰብ ቢችልም ቀደም ብለው ከ20ኛው እስከ 26ኛው ሳምንት በተከናወኑ መርሐግብሮች ያስመዘገባቸው ደካማ ውጤቶች አሁን ላለበት ውጥረት ዳርገውታል።

በመሆኑም በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን የቅርብ ተፎካካሪው ማሸነፍ በቀጣይ ሳምንታት ለመትረፍ በሚያደርገው ትንቅንቅ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ይህ እንዲሳካ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የማጥቃት አጨዋወቱን ማሻሻል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ቡድኑ ከተጋጣሚው አሁናዊ ብቃት አንፃር በነገው ጨዋታ እንደ ባለፉት  ሳምንታት ጠንከር ያለ የመከላከል ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም ባለፉት ሰባት መርሐግብሮች ላይ ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው እና በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ ጉልህ ክፍተቶች የተስተዋለበትን የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ የማድረግ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።

እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ሰላሣ ስምንት ነጥብ ሰብስበው በወራጅ ቀጠናው አፋፍ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ከዘጠኝ መርሐግብሮች በኋላ ድል አድርገው መጠነኛ እፎይታ ለማግኘት የቅርብ ተፎካካሪያቸውን ይገጥማሉ።

ጉልህ የወጥነት ችግር የተስተዋለበት የውድድር ዓመት ያሳለፉት ዐፄዎቹ ከ22ኛው እስከ 24ኛው ሳምንት በተከናወኑ ሦስት መርሐግብሮች ላይ ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ደረጃቸው በማሻሻል 5ኛ ላይ መቀመጥ ቢችሉም ቀጥለው በተካሄዱ ጨዋታዎች ከድል ጋር መራራቃቸውን ተከትሎ የወራጅነት ስጋት እንዲያንዣብብባቸው ሆኗል። በ25ኛው ሳምንት 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከነበረው ባህር ዳር ከተማ በአራት ነጥቦች ርቀት ላይ የነበረው ቡድኑ ባለፉት ዘጠኝ መርሐግብሮች ማሳካት ከሚገባው ሀያ ሰባት ነጥብ አምስቱን ብቻ ማሳካቱም ያለበትን አሁናዊ ብቃት ማሳያ ነው።

በመጨረሻው መርሐግብር በወላይታ ድቻ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ነገው ወሳኝ ጨዋታ የሚቀርቡት ፋሲሎች ካሉበት አጣብቂኝ ለመውጣት በብዙ ረገድ መሻሻል ይኖርባቸዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስተናገደውና መዋቅራዊም ሆነ ግለ-ሰባዊ ድክመት የተስተዋለበት የመከላከል አደረጃጀቱ ግን አንገብጋቢ መፍትሔ ይሻል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከኋላ መስመር ያሉባቸውን ችግሮች ከመቅረፍ ባለፈ አጠቃላይ የቡድኑ ስሜትና የአሸናፊነት መንፈስ ከፍ ማድረግ የሚችሉ ስራዎች መስራትም በውጤቱ ላይ አወንታዊ አስተዋጾ እንደሚኖረው ይታመናል። ይህ የማነሳሳት ስራቸው ደግሞ ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ የነበረው ስሜት ከመቀየር አኳያ ይበልጥ አስፈላጊ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባለፈ ግን ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያለው ውስንነት ማሻሻል እንዲሁም በቁጥር በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥርበት ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅበታል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሽመክት ጉግሳ ከቅጣት ቢመለስም አሸናፊ ጥሩነህ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አብዱላሂ አላዮ አሁንም በጉዳት የማይኖር ሲሆን የቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በፋሲል ከነማ በኩል ኢዮብ ማቲያስ ከጉዳት ማርቲን ኪዛ ከቅጣት ሲመለሱ ሀብታሙ ተከስተ ግን በቅጣት አሁንም አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 8 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ 4 ጊዜ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጎል ረገድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 12 ፋሲል ከነማ ደግሞ 11 ግቦች አስቆጥረዋል።