ከአትዮጵያ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ቅሬታውን ለአለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ሲዳማ ቡና አቤቱታውን ተቋሙ መቀበሉን የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ ለሶከር ኢትዮጵያ በላኩት መረጃ ገልፀዋል።
የ2017 የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ መካከል ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ተካሂዶ ሲዳማ ቡና 2ለ1 በማሸነፍ የተዘጋጀለትን ዋንጫ በወቅቱ ማንሳቱ ይታወሳል። ሆኖም ከቀናቶች በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በተቋቋመው የፋይናንስ አጣሪ ኮሚቴ ክለቡ የፋይናንስ ደንብ ጥሰትን ከፈፀሙ አራት ክለቦች አንዱ ነው በሚል ያቀረበውን ክስ ከመረመረ በኋላ ቡድኑ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ ዋንጫን ለወላይታ ድቻ ተላልፎ እንዲሰጥ እና ቡድኑን ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ እንዲሳተፉ መወሰኑም ይታወቃል።
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ “አሸንፌ የወሰድኩትን ዋንጫ ልነጠቅ አይገባኝም” በማለት አስቀድሞ ለፌድሬሽኑ በኋላም ደግሞ ለአለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ (CAS) ሐምሌ 4/2017 ዝርዝር ጉዳዮችን በመጥቀስ በደብዳቤ ይግባኝ ብሎ እንደነበር ይታወሳል። የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጃጎ አገኘሁ ማምሻውን ለሶከር ኢትዮጵያ በስልክ እንደገለፁት ከሆነ ያስገቡትን የቅሬታ ደብዳቤን በዛሬው ዕለት ካስ መቀበሉን እንዲሁም ለፊፋ እና ካፍ በአንፃሩ በግልባጭ ተቋሙ ስለ ማሳወቁ ነግረውናል።
